አፈታሪክ የሚመስለው የዴቪድ ራያ እድገት

AMN- ግንቦት 21/2018 ዓ.ም

ዴቪድ ራያ ይቅበጠበጣል ፤ ጓንቶቹን አጥልቆ በረጅሙ ተነፈሰ። እንደዚህ የተዘጋጀው የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ ጨዋታ ሊያከናውን አይደለም። ይልቁንም በናሽናል ሊግ (አምስተኛ ዲቪዚዮን) ለሚወዳደረው ሳውዝፖርት የመጀመሪያ ጨዋታውን ለማድረግ እንጂ።

ስፔናዊው ወጣት ግብ ጠባቂ እንደዚያ የተጨነቀበትን ጨዋታ በሽንፈት ደመደመ። ከ12 ዓመታት በፊት ከ1,500 ባነሰ ተመልካች ፊት ሳውዝፖርት በማክልስፊልድ 3 ለ 0 ሲሸነፍ የእግርኳስ ሕይወት ምን እንደምትመስል የቀመሰው ራያ ያ ጨዋታ ትልቅ ስንቅ ሆኖታል።

አሁን 30 ዓመቱ ላይ የሚገኘው ራያ የአርሰናል አለኝታ እስኪሆን ድረስ በርካታ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል። ዴቪድ ራያ ዕድሜው 16 ዓመት እስኪሆነው ድረስ በባርሴሎና ዳርቻ በሚገኝ ኮርኔያ በተባለ የሦስተኛ ዲቪዚዮን ክለብ ወጣቶች ቡድን ይጫወት ነበር።

ከዛም የሕይወትን ሌላ መልክ ለመመልከት ወደ እንግሊዝ አቀና። የላንክሻየሩ ክለብ ብላክበርን ደግሞ ለሙከራ የተቀበለው ክለብ ሆነ። ራያ ምንም እንኳን ብላክበርን ይቀበለው እንጂ ለትውልድ ከተማው ክለብ ኮርኔያ ወጣት ቡድን እንኳን የመጀመሪያ ተመራጭ አልነበረም። በ2012 ብላክበርን ከፕሪሚየር ሊጉ በወረደበት የውድድር ዘመን የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ ፖል ሮቢንሰን ፣ ጄክ ኪን እና ሲሞን ኢስትዉድ የክለቡ ግብጠባቂዎች ነበሩ።

ሁኔታው ያላማረው ራያ ወደ ፊት ያራምደኛል ብሎ ያሰበውን ውሳኔ አሳለፈ። ሶስት ሊግ እርከኖችን ወርዶ በአምስተኛ ዲቪዚዮን ለሚወዳደረው ሳውዝፖርት በውሰት ፈረመ። በዚያም አራት ወራትን ቆይቶ የተሻለ ልምድ ማግኘት ቻለ።

ራያ በሳውዝፖርት በሳምንት ሦስት ቀን ብቻ ይሰለጥን ነበር ፤ ፕሮፌሽናል ለመሆን ህልም ላለው ግብ ጠባቂ ይህ በቂ ስላልሆነ ሳውዝፖርት ልምምድ በማይኖረው ቀን ወደ ብላክበርን እየተመለሰ ይሰለጥን ነበር።

ዳቪድ ራያ የሳውዝፖርት ቆይታው በተለይ በረጃጅም የሚጣሉ የአየር ላይ ኳሶችን እንዴት መከላከል እንደሚችል ልምድ ቀስሟል። ምንም እንኳን 1.83 ሜትር ቢረዝምም ቅልጥፍናው እና ጊዜ አጠባበቁ አስደናቂ እንደነበር በወቅቱ አብረውት የሰሩ አሰልጣኞች ለቢቢሲ ስፖርት ተናግረዋል።

ግብ ጠባቂው በእግር የመጫወት ክህሎቱም አድናቆት እንዲቸረው አድርጎታል። በተለይ በሳውዝፖርት እያለ የቡድን አጋሮቹ ግብ ጠባቂነት እጣፈንታህ አይደለም ውጣ እና ተጫወት እያሉ ይቀልዱ ነበር። በእርግጥ ራያ በእግር የመጫወት ብቃቱን በተጫወተባቸው ክለቦች አሳይቷል። በታዳጊነቱ የፉትሳል ተጫዋች መሆኑ ለዚህ አግዞታል።

ራያ ወደ ብላክበርን ተመልሶ በሻምፒዮንሺፑ ላይ ጥቂት ጨዋታዎችን ቢያደርግም እስከ 2017 የክለቡ ቀዳሚ ተመራጭ አልነበረም። ብላክበርን ወደ ሊግ 1 (ሦስተኛ ዲቪዚዮን) ሲወርድ ቦታውን አስከበረ። ብላክበርን ዳግም ወደ ሻምፒዮንሺፕ እንደሚለስም ከፍተኛ አስተዋጽኦ አደረገ። ብቃቱም ለብሬንትፎርድ እንዲፈርም ዕድሉን ሰጠው።

ስፔናዊው ግብጠባቂ በ2019 ሶስት ሚሊየን ፓውንድ ተከፍሎበት ብሬንትፎርድን ተቀላቀለ። የመልማዮችን አይን ይበልጥ የሳበው በብሬንትፎርድ የነበረው የአራት ዓመት ቆይታ ነው። አርሰናል በተለይ ዋና አሰልጣኙ ሚኬል አርቴታ ወደ ፊት ያሻግረኛል ብሎ በማሰብ ግብ ጠባቂው መዳረሻው ሰሜን ለንደን እንዲሆን አድርጓል። ራያ በመድፈኞቹ ቤት በውሰት አንድ ዓመት ከቆየ በኋላ ከዚያም በ27 ሚሊየን ፓውንድ በቋሚነት ፈርሟል።

አርሰናል ዳቪድ ራያን ካገኘ በኋላ ስለ ግብ ጠባቂ ተጨንቆ አያውቅም ፤ ለአርሰናል ከ22 ዓመታት በኋላ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ ማንሳት ያለ ዴቪድ ራያ የሚታሰብ አልነበረም።

የፅናት ተምሳሌት የሆነው ራያ ከአምስተኛ ዲቪዚዮን ተነስቶ የፕሪምየር ሊግ ዋንጫ አሸናፊ ሆኗል። ታሪኩ በዚህ ብቻ አያበቃም ። ነገ በአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ዋንጫውን አንስቶ የማያውቀው አርሰናል ፓሪሰን ዠርማን ሲገጥም እንዲያሸንፍ ካገዘ ስሙን ዘላለማዊ ያደርጋል።

በሸዋንግዛው ግርማ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review