AMN – ግንቦት 25/2018 ዓ.ም

7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ነፃ እና ዴሞክራሲያዊ እንደነበር የተለያዩ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ ዕጩ ተወዳዳሪዎች ገለጹ።
ትላንት የተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ከንጋት 12:00 ሰዓት ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት ድረስ በነበረው ሂደት፣ የተለያዩ የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ዕጩ ተወዳዳሪዎች፣ የግል ተፎካካሪዎችና መራጩ ሕዝብ በንቃት በመሳተፍ የዜግነት ግዴታቸውን ተወጥተዋል።

የፖለቲካ አመራሮችና ዕጩዎች ሂደቱን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት፤ ምርጫው ነፃና ገለልተኛ መሆኑን ጠቅሰው የሕዝቡ ተሳትፎ ከፍተኛ እንደነበር አረጋግጠዋል።

በንፋስ ስልክ ላፍቶ ምርጫ ክልል በመካኒሳ ጤና ጣቢያ ተገኝተው ድምጻቸውን የሰጡት የሕዳሴ ፓርቲ ሥራ አስፈፃሚ አቶ ሀብታሙ አያሌው ፣ በምርጫው የታየውን ሰላማዊነትና የኅብረተሰቡን ከፍተኛ ተሳትፎ አድንቀዋል።

የኅብረት ለዴሞክራሲ እና ለነፃነት ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ መሀመድ አድን በበኩላቸው ፣ የምርጫው ሂደት እጅግ አበረታች እንደነበር ጠቅሰው፤ መራጩ ሕዝብ ይህንን ታሪካዊ ዕድል በመጠቀም በነቂስ ወጥቶ ድምፁን ሰጥቷል ብለዋል።

ሂደቱ ፍጹም ነፃ እንደነበር የገለጹት አቶ ኃይለማርያም ብርሃኑ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) የሰሜን ኢትዮጵያ አስተባባሪ፣ ኅብረተሰቡ ድምጹን ያለምንም ተጽዕኖ መስጠቱን ተናግረዋል፡፡
በበረከት ጌታቸው