የእንጦጦ ቀጨኔ የወንዝ ዳርቻ ለአእምሮም ለአካልም እረፍት የሚሰጥ ተወዳጅ አካባቢ ሆኗል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN – ግንቦት 25/2018 ዓ.ም

ከእንጦጦ እስከ ፒኮክ ከተዘረጉት ስድስት የዲዛይን ክፍሎች መካከል የመጀመርያው የሆነውና ከእንጦጦ እስከ ቀጨኔ መድኃኔዓለም የተዘረጋው የ9.6 ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ እና መልሶ ማልማት ፕሮጀክት ተጠናቆ ዛሬ በይፋ ተከፍቷል።

የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ እንደገለጹት ፣ ፕሮጀክቱ በስፋቱ 600 ሄክታር መሬትን ያካተተ ሲሆን፣ የአረንጓዴ ልማት አሻራ ጎልቶ የታየበት፣ ለጤና እጅግ አስፈላጊና ለአእምሮም ለአካልም እረፍት የሚሰጥ ተወዳጅ አካባቢ ሆኖ መገንባቱን ገልጸዋል።

ይህ ስፍራ ቀደም ሲል በተፈጥሮ የተሰጠ ቢሆንም በአግባቡ ባለመያዙና በደረሰበት የደን ጭፍጨፋ እና ብክለት ምክንያት ምቹ ወደ አልሆነ የተበከለ አካባቢነት ተቀይሮ እንደነበር ከንቲባዋ አስታውሰዋል።

ይሄ ቦታ ነዋሪዎች በክረምት በጎርፍ ውሃ እየተወሰዱ የሚሰቃዩበት፣ ከፍተኛ ብክለትና ከተላላፊ በሽታዎች መስፋፋት ጋር ተያይዞ ሕዝብ የሚሰቃይበት ስፍራ እንደነበር የዩኒቨርሲቲ ጥናቶችና የጤና መረጃዎች እንደሚያሳዩም ከንቲባዋ ገልጸዋል፡፡

ዛሬ ላይ በከፍተኛ ጥረትና ትጋት ቦታውን ሙሉ በሙሉ በመቀየር፤ የደረቁ ውሃዎች የፈልቁበት፣ የአፈርና ዳርቻ ጥበቃው በአግባቡ ተሰርቶ እጽዋት እንደ አዲስ አቆጥቁጠው ወደ ለምለምነት በመቀየሩ ለሰዎች እረፍት የሚሰጥ ስፍራ መሆኑን ገልጸዋል።

ቀደም ሲል ፕሮጀክቱን ለመስራት ከአንድ የውጭ ሀገር መንግስት ጋር ውል ተገብቶ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባዋ ፣ ሆኖም ኮንትራክተሩ በአምስት ዓመት ውስጥ አምስት ኪሎ ሜትር ለመገንባት ቃል ገብቶ የሁለት ኪሎ ሜትር የወንዝ ዳርቻ ጥበቃ ስራ እንኳን ሳይሰራ ጊዜው ማለቁን ጠቁመዋል።

ይህንን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባስተላለፉት አቅጣጫ መሰረት የከተማ አስተዳደሩ ስራውን በቁርጠኝነትና በእልህ መረከቡን ገልጸው፤ የወንዝ ዳርቻ ልማት ሰፊ ልምድ ባይኖረንም፤ ለሀገራችን ቅናት፣ እልህና ትጋት ስላለን ስራውን ማሳካት ችለናል ብለዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review