AMN – ግንቦት 26/2018 ዓ.ም
የእንጦጦ-ቀጨኔ ፕሮጀክት የአካባቢውን ማህበረሰብ ባህልና ታሪክ ከማክበሩም በላይ፣ ባለፉት ዘመናት ለሸማኔና ሸክላ ጥበብ ባለሙያዎች ይሰጥ የነበረውን አግላይና አሳፋሪ አስተሳሰብ የቀየረ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ፕሮጀክቱ በአካባቢው ለሚገኙ ከ10 ሺህ በላይ ነዋሪዎች፣ በጠቅላላው መስመር ደግሞ እስከ 56 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የስራ ዕድል መፍጠሩን ተናግረዋል፡፡
በቀጨኔ መድኃኔዓለም፣ በእንጦጦ እና በጉለሌ አካባቢዎች የተከናወነው የመልሶ ማልማት እና የወንዝ ዳርቻ ልማት ፕሮጀክት፣ የአካባቢውን ነዋሪዎች ታሪክ፣ ባህልና ሙያ ያከበረና ዘላቂ ተጠቃሚነትን ያረጋገጠ መሆኑን ገልጸዋል።
ከንቲባዋ እንደተናገሩት ፣ ፕሮጀክቱ ቀደም ሲል በአካባቢው በሚኖሩ የሸማ እና የሸክላ ጥበብ ባለሙያዎች ላይ ይንጸባረቅ የነበረውን አግላይ አስተሳሰብ የለወጠ ነው።

የሙያ ውጤታቸውን እየወደድን ሙያተኛውን ግን የምንሰድብበትና የምናቃልልበት ትክክል ያልሆነ አሳፋሪ አስተሳሰብ ነበረን፤ አሁን እሱን ጭምር ነው ያደስነው” ሲሉ ከንቲባዋ ገልጸዋል።
የአካባቢውን ጥበብ ለማስታወስና ለማስተዋወቅ አክንባሎ ሬስቶራንት የተሰኘ ውብ ማዕከል መገንባቱን የገለጹት ከንቲባ አዳነች ፤ ማዕከሉ የእጅ ጥበብ ስራዎች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ቱሪስቶች የሚሸጡበትና የስራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ጠቁመዋል።
የሽመና እና የሸክላ ስራ ጥበብን የሚወክሉ ሀውልቶችና መታሰቢያዎችም በስፍራው መቆማቸውን ጠቅሰው፣ መልዕክቱም ስራችሁ ክቡር እንጂ የሚታፈርበት አይደለም የሚል መሆኑን አስገንዝበዋል።
የአካባቢው ማህበረሰብ ቀደም ሲል ማዶ ለማዶ ለመገናኘት በበጋ ወቅት ግንድ በማጋደም፣ በክረምት ደግሞ በጎርፍ የመወሰድ አደጋ ይጋረጥበት እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባዋ ፣ ዛሬ ግን ያ አስቸጋሪ ታሪክ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል ብለዋል።

የአካባቢው ማህበረሰብ በልማቱ እጅግ ደስተኛ መሆኑንና ከልማቱ ጎን መቆሙንም ገልጸዋል።
እስከ ፒኮክ ባለው አጠቃላይ የወንዝ ዳርቻው የልማት መስመር ላይ እስከ 56 ሺህ የሚደርሱ ዜጎች የስራ ዕድል ማግኘታቸውም ተመላቷል፡፡
የተገነቡት ካፌዎችና ሬስቶራንቶች እንደ “መርከብ”፣ “አክንባሎ” እና “ተንጠልጣይ” ያሉ የአካባቢውን መገለጫዎችና ካራክተር የያዙ ናቸው።
በፍሬሕይወት ብርሃኑ