AMN – ግንቦት 26/2018 ዓ.ም

ምርጫ የሐሳብ ፍልሚያ የሚስተናገድበት፣ የፓርቲዎች አማራጭ ለሕዝብ የሚቀርብበትና በነፃ የድምፅ አሰጣጥ ሂደት አሸናፊው የሚታወቅበት ዴሞክራሲያዊ መድረክ ነው።
ይሁንና የአንድ ምርጫ እውነተኛ ስኬት የሚረጋገጠው በሂደቱ ፍትሐዊነት ብቻ ሳይሆን በምርጫው ማግስት የሚመጣውን ውጤት ተከትሎ ተፎካካሪዎችና ደጋፊዎቻቸው በሚያሳዩት ሰላማዊ አቀባበል ነው።

ኢትዮጵያ 7ኛውን ሀገራዊ ጠቅላላ ምርጫ ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በስኬት አጠናቃ፤ ቀጣዩን ምዕራፍ በመጠባበቅ ላይ ትገኛለች።
ይንን ተከትሎ ኤ ኤም ኤን ያነጋገራቸው ወጣቶች፣ ውጤትን በጸጋ መቀበል ለሀገር ኅልውና እና ለዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ዋነኛው መሠረት መሆኑን ገልጸዋል።

የሕዝብን የድምፅ ብልጫ ያገኘው የፖለቲካ ፓርቲ ሀገር የመምራት ዕድል ማግኘቱን አምኖ መቀበል የበሰለ ፖለቲካ መገለጫ መሆኑን የገለጹ ሲሆን አሸናፊው ለሀገር የሚበጅ እስከሆነ ድረስ የሕዝብን ድምፅ ማክበርና ለቀጣይ ዝግጅት ማድረግ ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
በቀጣይ የምርጫ ውጤት ይፋ ከሆነ በኋላ በተለይም ወጣቱ ማኅበረሰብ ሊኖረው የሚገባውን ሚና የገለጹት ወጣቶቹ የተመረጠው አካል ጠንካራ ጎኖቹን እንዲያስቀጥልና ደካማ ጎኖቹ ደግሞ በምክክርና በውይይት እንዲታረሙ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

የሚቀጥሉትን አምስት ዓመታት ስኬታማ ለማድረግም የሚመጣውን መንግስት መደገፍ፣ ማገዝ እና እያንዳንዱ ዜጋ በየተሰማራበት የሥራ መስክ ሀገሩን በታማኝነት ማገልገል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ወጣቶቹ እራሳቸውን በዘመናዊና በሰለጠነ አስተሳሰብ በማነጽ፣ አሸናፊውን አካል ተቀብለው ኢትዮጵያን ወደፊት ለማስቀጠል የሚኖራቸው ዝግጁነት ለነገዋ ኢትዮጵያ ትልቅ ተስፋ ነው።
በትዝታ መንግስቱ