AMN – ግንቦት 27/2018 ዓ.ም

7ኛውን ጠቅላላ ምርጫ ለማደናቀፍ የተሳሳቱ ፕሮፓጋንዳዎች ሲነዙ ቢቆዩም ኢትዮጵያን ማጽናትና መጻኢ ዕድሏን መወሰን የሚቻለው በምርጫ ብቻ መሆኑን ሕዝቡ በድምጹ አሳይቷል።
ግንቦት 24 የተካሄደው ድምፅ አሰጣጥ በታላቅ ስኬት ተጠናቆ በየደረጃው ውጤት የማሳወቅ ሂደት እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሚወዳደሩበት በሻሻ ተገኝተው ድምፅ በሰጡበት ወቅት እንደገለጹት ፣ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ሕዝቡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዲሞክራሲያዊ ምርጫ ማድረግ አይቻልም” የሚል እምነት እንዲያዝ ሰፊ የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ሲያሰራጩ ሰንብተው ነበር።

ነገር ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሁሌም እንደሚያደርገው በወሳኝ ታሪካዊ ሁነቶች ወቅት የሚያሳየውን ከፍተኛ የጀግንነት መንፈስ በድጋሚ አስመስክሯል ብለዋል።

በዕለቱ ከማለዳ ጀምሮ በመሰለፍ ምርጫውን በስኬት አካሂዷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ እርምጃ ሕዝባችን ሀገረ መንግሥቱን ለመገንባትና የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ፍላጎቱን ለመወሰን መካሪና ገሳጭ እንደማያስፈልገው ያሳየበት ነው ሲሉ አብራርተዋል።
በተመሳሳይ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ “ዲሞክራሲ አይገባህም፤ እኛ እናውቅልሃለን” በሚሉ የተለያዩ ውጫዊ ተጽዕኖዎች፣ ጉትጎታዎችና ማስፈራሪያዎች ሲፈተን የቆየው ሕዝብ፣ ለሀገሩ ያለውን ታላቅ ጽናትና ጥልቅ ፍቅር በተግባር ያሳየበት ታሪካዊ ዕለት መሆኑን ገልጸዋል።

የምርጫው አጠቃላይ ሂደትን የታዘቡት የሀገር ውስጥ የሲቪል ማህበራት ፣ የአፍሪካ ኅብረት እና የኢጋድ ቡድኖች በነበራቸው ቆይታ የተሳካ ምልከታ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
የአፍሪካ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪና የቀድሞው የኬንያ ፕሬዚዳንት ኡሁሩ ኬንያታ፣ ዜጎች ያለምንም ተፅዕኖ የፈለጉትን ፓርቲ በነፃነት መምረጣቸውን ገልጸው፣ ሂደቱ ለመላው አፍሪካ የዲሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ተምሳሌት የሚሆን ነው ብለዋል።

የኢጋድ የምርጫ ታዛቢ ቡድን መሪ ስፔሲዮዛ ዋንዲራ ካዚብዌ (ዶ/ር)፣ በምርጫው ሂደት ላይ የታየውን ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ አድንቀዋል።
ግንቦት 24 አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ከማለዳው 12 ሰዓት ጀምሮ እስከ እኩለ ሌሊት 6 ሰዓት ድረስ በጽናት ቆመው ድምፅ በመስጠት ታሪክ ሰርተዋል።
በተለይም እናቶች፣ አዛውንቶች እና አካል ጉዳተኞች በከፍተኛ ንቃትና ተነሳሽነት በመሳተፍ ለዲሞክራሲ መዳበር ያላቸውን ቀናኢነት በተግባር አሳይተዋል፡፡
በትዝታ መንግስቱ