አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ መስጠት ተጀመረ

You are currently viewing አዲሱ የተሽከርካሪ ሰሌዳ መስጠት ተጀመረ

AMN – ሰኔ 04/2018 ዓ.ም

የአሽከርካሪና ተሽከርካሪ ፈቃድና ቁጥጥር ባለስልጣን አዲሱን ሰሌዳ በአዲስ ተሽከርካሪዎች ላይ ከዛሬ ጀምሮ ተግባራዊ ማድረግ ጀመረ።

አዲሱ ሰሌዳ፣ ከዚህ ቀደም ከሰሌዳ አመራረት ምቹ አለመሆን እና ከስርጭት ጋር ተያይዞ የሚፈጠሩ ተግዳሮቶችን ጨምሮ ለሀሰተኛ ስራ ተጋላጭነትንና ሌሎች ጉድለቶችን ለመቅረፍ በማለም ማስፈለጉን የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘገየ በላይ ገልጸዋል።

አዲሱ ሰሌዳ አሰጣጥ ተመዝግበው ሰሌዳ በመጠባበቅ ላይ ባሉ ተሽከርካሪዎች ላይ የሚጀምር ሲሆን፤ ሰሌዳው ወጥነት ያለው፣ ዓለም አቀፍ ጥራቱን፣ ሀገራዊ ይዘቱን የጠበቀና ለህግ ማስከበር ስራ አመቺ መሆኑ ተገልጿል።

በተጨማሪም አንድ ጊዜ የተሰጠ ሰሌዳ ተሽከርካሪው አገልግሎት መስጠት እስኪያቆም ድረስ የሚያገለግል መሆኑ ተብራርቷል።

የትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስትር አማካሪ አቶ አሰፋ ሀዲስ በበኩላቸው፣ አዲሱ ሰሌዳ “ETH” የሚል ዓለም አቀፍ ኮድ ያለው መሆኑን ገልጸው፣ ሥርዓቱ በትራንስፖርትና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር የለማ መሆኑን አብራርተዋል።

ይህ አዲስ አሰራር ሰሌዳ መፍታትን የሚያስቀርና ሙሉ የተሽከርካሪው መረጃ የሚገኝበት ሲስተም መሆኑንም ነው የገለጹት።

የሰሌዳውን ዋጋ በተመለከተ እንደ ተሽከርካሪው ዓይነትና አገልግሎት ልዩነቶች መኖራቸው የተገለጸ ሲሆን፣ ድጎማና ማበረታቻዎች እንደተካተቱበትም ተመላክቷል።

የመጀመሪያው “00” (ዜሮ ዜሮ) ታርጋ በየካ ቅርንጫፍ መሰጠት ተጀምሯል።

ቤተልሔም አየነው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review