ምክር ቤቱ የአየር አገልግሎት ረቂቅ አዋጆችን መርምሮ አጸደቀ

AMN ግንቦት 27/2018

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 23ኛ መደበኛ ስብሰባ ኢትዮጵያ ከተለያዩ ሀገራት ጋር ያደረገቻቸውን የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጆች መርምሮ አጸደቀ።

የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ምክትል ሰብሳቢ ፈትሂ ማሕዲ (ዶ/ር) የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጆችን ሪፖርትና የውሳኔ ሐሳቦች ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡

በዚሁ ወቅትም፤የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጆቹ ኢንቨስትመንትን በመሳብና የአየር ትራንስፖርት መዳረሻዎችን በማስፋት ለሀገራችን የአየር ትራንስፖርትና ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ያላቸው ሚና ወሳኝ ነው ብለዋል።

ከአየር አገልግሎት ስምምነቶቹ መካከልም በኢትዮጵያ መንግሥትና እና በሴራሊዮን መንግሥት በኩል የተፈረመው አንዱ መሆኑን ጠቁመው፤ ስምምነቱ ለአየር መንገዶች ወደ ተመረጡ መዳረሻዎች በቀጥታ ለማረፍና ምቹ የአቪዬሽን አገልግሎት እንዲሰጡ እንደሚያስችል አስገንዝበዋል።

ይህን የአየር አገልግሎት ረቂቅ አዋጅም፤ ምክር ቤቱ አዋጅ ቁጥር 1417 /2018 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በተመሳሳይ በአንጎላ ሪፐብሊክ እና በኢትዮጵያ መንግሥት መካከል የተፈረመው የአየር አገልግሎት ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ለምክር ቤቱ የቀረበ ሲሆን፤ ስምምነቱ በሀገራቱ መካከል ያለውን በርካታ ዓመታት ያስቆጠረ ግንኙነት ለማሳደግ ዕድል ይፈጥራል ብለዋል።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መረጃ እንዳመላከተው፤ ይህ ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1418 /2018 ሆኖ በሙሉ ድምጽ ፀድቋል።

በሌላ በኩል በኢትዮጵያ መንግሥት እና በባንግላዴሽ መካከል የተደረገው የአየር አገልግሎት ስምምነት በሀገራቱ መካከል እያደገ የመጣውን የአየር ትራንስፖርት ፍሰት ከግምት ያስገባ መሆኑንም ነው ያነሱት።

አክለውም፤ የውጪ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ለመሳብ፣ በንግድ፣ ቱሪዝም እና የውጪ ምንዛሬ ለሀገራችን በማስገኘት ረገድ ጉልህ ሚና ይኖረዋል ብለዋል፡፡

በዚህም መሠረት ምክር ቤቱ ይህን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1419/ 2018 አድርጎ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

ሌላው በምክር ቤቱ የጸደቀው የአየር አገልግሎት ረቂቅ አዋጅ፤ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኢስዋቲኒ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት መካከል የተደረገው ስምምነት ነው።

ይህም ያለ በረራ ድግግሞሽ ገደብ የጭነት በረራዎችን ማከናወንን ጨምሮ ለበረራ የሚያስፈልጉ ቁሳቁሶችን ከጉምሩክ ቀረጥ ነፃ ማስገባትን የሚያካትት በመሆኑ፤ የበረራ ወጪን እንደሚቀንስ አስረድተዋል።

በተመሳሳይ ምክር ቤቱ ይህን ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1420/2018 አድርጎ በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የአየር አገልግሎት ስምምነቶቹ፤ የኢትዮጵያን ጥቅም የሚያስጠብቁና በዘርፉ በቀጣናው ያላትን ሚና በማጉላት ተጠቃሚነቷን የሚያሳድጉ መሆናቸው ተመላክቷል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review