በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው የሕዝብ ተሳትፎ የማኅበረሰቡን የዲሞክራሲ ግንዛቤ ማደግ ያሳየ መሆኑ ተገለጸ

You are currently viewing በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው የሕዝብ ተሳትፎ የማኅበረሰቡን የዲሞክራሲ ግንዛቤ ማደግ ያሳየ መሆኑ ተገለጸ

AMN – ግንቦት 28/2018 ዓ.ም

በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው የሕዝብ ተሳትፎ የማኅበረሰቡን የዲሞክራሲ ግንዛቤ ማደግ ያሳየ ነው ሲሉ የፌደራሊዝምና ገቨርናንስ ምሁር ተስፋዬ ጅማ (ዶ/ር) ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያውያን በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ለዲሞክራሲ ያላቸውን አመለካከትና ቁርጠኝነት ለዓለም የመሰከሩበት ታሪካዊ ቀን ነው፡፡

ዲሞክራሲያዊ መብታቸውን በመጠቀም በነቂስ ወጥተው ድምጻቸውን የሰጡ መራጮች በአሁኑ ወቅት የምርጫውን ውጤት በከፍተኛ ጉጉት በመጠባበቅ ላይ ናቸው።

የምርጫው ሂደትና ስለ ዲሞክራሲ ግንባታ ጉዞ ከኤ ኤም ኤን ጋር ቆይታ ያደረጉት የፌደራሊዝምና ገቨርናንስ ምሁር ተስፋዬ ጅማ (ዶ/ር)፣ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ የታየው የሕዝብ ተሳትፎ፣ የማኅበረሰቡ የዲሞክራሲ ግንዛቤ ማደጉንና መበልጸጉን በግልጽ ያሳየ ነው ብለዋል፡፡

ሕዝቡ ምርጫ ምን ማለት እንደሆነ እየተረዳ መምጣቱን የገለጹት ምሁሩ፣ እስከ እኩለ ለሊት ድረስ በነቂስ ወጥቶ፣ ‘ይበጀኛል፣ ይመራኛል’ ያለውን ፓርቲ መርጧል ብለዋል።

በዚህም ድምፁ ዋጋ እንዳለው ትልቅ መልዕክት አስተላልፏል ነው ያሉት።

የዘንድሮው ምርጫ ኢትዮጵያ እስከ አሁን ካካሄደቻቸው ጠቅላላ ምርጫዎች በብዙ መመዘኛዎች የተለየ እንደነበር በማንሳትም፣ ይህም ከፍተኛ የመራጮች ቁጥር፣ ሰፊ የታዛቢ ሽፋን መሰጠቱ ልዩ እንደሚያደርገው ገልጸዋል።

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ነፃና ገለልተኛ ሆኖ የተዋቀረ ተቋም በመሆኑ ምርጫውን በሰላማዊ እና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መልኩ ማካሄድ ችሏል የሚሉት ምሁሩ፣ ከ170 በላይ የሲቪክ ማኅበራት ዕውቅና አግኝተው፣ በመላው ሀገሪቱ ምርጫውን መታዘባቸውን ጠቁመዋል።

የዲሞክራሲ ልምምድ ከሚደርግባቸው ዋና መንገዶች አንዱ ምርጫ መሆኑን በመግለጽም፣ ማንኛውም አካል ወደ ሥልጣን መምጣት ያለበት የሕዝብን ፈቃድ በማግኘት ነው ብለዋል።

ሕዝቡ ለወደፊቱ አምስት ዓመታት ሀገሪቱን የሚመራ አካል በድምጹ መርጧል ያሉት ምሁሩ፣ ውጤቱን በጸጋ መቀበል እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

በወርቅነህ አቢዮ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review