AMN – ሰኔ 2/2018 ዓ.ም
ቢሮክራሲ በዘመናዊው የመንግሥት አስተዳደር አውድ ውስጥ የመንግሥት አገልግሎቶችን ተደራሽ ከማድረግ፣ የልማት ስትራቴጂዎችን ከማስፈጸም፣ የሕግ የበላይነትን ከማስከበርና ከመቆጣጠር፣ መረጃዎችንና ታሪካዊ ሰነዶችን ከመሰነድና መሰል ተግባራትን ከማስፈጸም አንጻር ያለው ሚና የጎላ ነው።
የኢትዮጵያ ቢሮክራሲ ለሀገሪቱ ያበረከተው ጠቀሜታ እንደየዘመኑና እንደየወቅቱ ሁኔታ የሚለያይ ቢሆንም፣ እስከ ቅርብ ዓመታት ድረስ ዘርፉ ለሕዝብ ቅድሚያ ከመስጠት፣ መልካም ሥነ ምግባርና የአገልጋይነት ስሜትን ከመላበስ ረገድ በርካታ ውስንነቶች ታይተውበት ቆይተዋል።

የሰው ኃይል ብቃት ማነስና የተሳለጠ የአሠራር ሥርዓት አለመኖር ቢሮክራሲውን ከሚፈትኑ ተግዳሮቶች መካከል ሌላኛው ሲሆን፣ ተገልጋዩ ሕብረተሰብ በእነዚህ ውስንነቶች ምክንያት አንድን ጉዳይ ለማስፈጸም ሰዓታትን፣ ቀናትን፣ ሳምንታትንና ወራትን ያለአግባብ ለማባከን ሲገደድ ቆይቷል።
ጊዜውን አባክኖ ጉዳዩን ማስፈጸም ያልቻለው ተገልጋይ ዘመድ አዝማድና ደላላን በማፈላለግ፣ አሊያም የእጅ መንሻ በመስጠት ጉዳዩን ሲያስፈጽም የነበረ ሲሆን፣ በዚህ አግባብ ጉዳይን ማስፈጸም እንደ ትክክለኛ አሠራር እስከመታየት ደርሶ ነበር።
የቢሮክራሲው ቀርፋፋነትና የጥራት ማነስ የወለዳቸው የመልካም አስተዳደር ችግሮች፣ ሙስናና ብልሹ አሠራሮች የመንግሥት አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ፣ የልማት ስትራቴጂዎችን ለማስፈጸም፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና ለመቆጣጠር ትልቅ እንቅፋት ሆነው ቆይተዋል።
ለዘመናት የዘለቀውን የኢትዮጵያን ቢሮክራሲ ስብራት ለመጠገን ቴክኖሎጂን መሠረት በማድረግ ባለፉት ጥቂት ዓመታት በተከናወኑ ተግባራት፣ አገልጋዩና ተገልጋዩ የማይገናኙበትን የአሠራር ሥርዓት መፍጠር ተችሏል።

ላለፉት በርካታ ዓመታት ሕዝብ ሲማረርበት፣ ዘመድ አዝማድ፣ ደላላና እጅ መንሻ ሲጠየቅበት የነበረውን የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ በደቂቃዎች ውስጥ መፈጸም የተቻለ ሲሆን፣ ተገልጋዩም ወደ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሳይመጣ ባለበት ሆኖ ጉዳዩን የሚጨርስበት አሠራር ተዘርግቷል።
በኢትዮጵያ የቢሮክራሲ ታሪክ ተገልጋዩ ሕብረተሰብ አገልግሎት ለማግኘት የመንግሥት ተቋማትን ደጅ የሚጠናበት አስቸጋሪው ምዕራፍ ተዘግቶ፣ የመንግሥት አገልግሎት ሰጪ ተቋማት አገልግሎታቸውን በአንድ መሶብ ሰንቀው በየተገልጋዩ ደጃፍ በመቆም አገልግሎታችንን ተቀበሉን የሚሉበት አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል።
ይህ በቴክኖሎጂ የታገዘው የመንግሥት አገልግሎት አሰጣጥ የተገልጋዮችን ጊዜ ከመቆጠቡና ለእጅ መንሻነት ይወጣ የነበረውን ተገቢ ያልሆነ የሕዝብ ሀብት ከማስቀረቱም በላይ፣ የልማት ስትራቴጂዎችን በአግባቡ ለመፈጸም፣ የሕግ የበላይነትን ለማስከበርና ለመቆጣጠር፣ መረጃዎችንና ታሪካዊ ሰነዶችን ከመሰነድ በተጨማሪ መሰል የመንግሥት አገልግሎቶችን በጥራት ለማከናወን አስችሏል።

በአዲስ አበባ የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል ዲጂታል የመንግሥት አገልግሎት ወደ ሁሉም ክፍለ ከተሞች የተስፋፋ ሲሆን፣ በሀገር አቀፍ ደረጃም በተለያዩ ክልሎችና ከተሞች ተግባራዊ በመደረግ ላይ ይገኛል።
በወንድማገኝ አሰፋ