AMN- ሰኔ 2/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ በመማር ማስተማር ሂደቱ ላይ የሚስተዋሉ የግብዓት እጥረቶችን ለመቅርፍና የትምህርት ጥራትን ለማረጋገጥ የሚያስችል የግብዓት ድጋፍ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤቶች አበርክቷል፡፡
ቢሮው በትምህርት ዘርፉ ተደራሽነትን በስፋት ከማሳደግ ጎን ለጎን፣ ጥራትን በአስተማማኝ ሁኔታ ለማስጠበቅ በርካታ ስኬታማ ተግባራትን እያከናወነ ይገኛል።

በተለይም የነገ ሀገር ተረካቢ የሆኑ ሕፃናት ስብዕና እና ዕውቀት የሚቀረጽበትን፣ እንዲሁም የትምህርት የመጀመሪያው መሠረት የሆነውን የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርትን በዘመናዊ ግብዓት የማደራጀት ሥራ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሚገኝ ተገልጿል።
ቀደም ሲል በዚህ ዘርፍ የተሰሩ የግብዓት ማሟላት ሥራዎች በሕፃናት ዕውቀት እና ክህሎት ላይ ተጨባጭና አዎንታዊ ውጤት ማምጣታቸውን የአዲስ አበባ ትምህርት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላዬ ዘውዴ ተናግረዋል።

ምክትል ኃላፊው አክለውም፣ አሁን የተደረገው የግብዓት ድጋፍ የመማር ማስተማር ሂደቱ ሕፃናት ይበልጥ እየተጫወቱ የሚማሩበት ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር ገልጸው፤ ሕፃናት ወደ ትምህርት ገበታቸው በፍቅር፣ በደስታና በከፍተኛ ተነሳሽነት እንዲመጡ ትልቅ መነቃቃትን እንደሚፈጥርላቸው አስገንዝበዋል።

በዕለቱ የድጋፍ ቁሳቁሶቹን የተረከቡት የክፍለ ከተማ ትምህርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች በበኩላቸው፣ የተደረገው ድጋፍ በትምህርት ቤቶች ውስጥ ዘመናዊ፣ ሳቢ እና ምቹ የመማሪያ አካባቢን ለመፍጠር ለተጀመረው አገራዊ ጉዞ ተጨማሪ አቅምና ትልቅ ስንቅ እንደሚሆን አስታውቀዋል።
በቴዎድሮስ ይሳ