ኢጋድ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት ለኢትዮጵያዊያን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፈ

You are currently viewing ኢጋድ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት ለኢትዮጵያዊያን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላለፈ

AMN- ሰኔ 16/2018

የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን (ኢጋድ) በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማነት ለኢትዮጵያዊያን የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በ7ኛው ጠቅላላ ምርጫ አብዛኛውን የምክር ቤት ወንበሮች ብልጽግና ፓርቲ ማሸነፉን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

ይሄንን ተከትሎ የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት ባለስልጣን ባወጣው መግለጫ ግንቦት 24 ቀን 2018 ዓ.ም. በተካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ምርጫ ስኬታማ አካሄድ ለኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፏል።

በምርጫው አብላጫ ድምፅ ያገኘውን ብልጽግና ፓርቲን እና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)ን እንኳን ደስ ያላችሁ ብሏል።

ኢጋድ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ ሂደቱን በመምራት ረገድ ላሳየው ሙያዊ ብቃትና ቁርጠኝነት ምስጋና ያቀረበ ሲሆን ምርጫው በሰላማዊና በሥርዓት እንዲጠናቀቅ ባደረጉት ተሳትፎም የኢትዮጵያን ሕዝብ አድንቋል።

የምርጫው በስኬት መጠናቀቅ ኢትዮጵያ ለዲሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታና ለሕገ-መንግሥታዊ ሥርዓቱ ያላትን ቀጣይነት ያለው ቁርጠኝነት የሚያንጸባርቅ ነው ብሏል።

ሀገሪቱ ብሔራዊ አንድነትን ለማጠናከር፣ አካታች ውይይትን ለማሳደግ እንዲሁም ሰላምን፣ መረጋጋትንና ዘላቂ ልማትን ለማስፈን ለምታደርገው ቀጣይ ጥረት ያለውን ድጋፍም ገልጿል።

ኢጋድ በቀጣናው ትብብርን፣ ውህደትን፣ ሰላምን፣ መረጋጋትንና ዘላቂ ልማትን ለማስቀጠል ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በቅርበት ለመሥራት ያለውን ቁርጠኝነት በድጋሚ ያረጋግጣል ሲል መልዕክቱን ማስተላለፉን ኢዜአ ዘግቧል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review