AMN – ሰኔ 21/ 2018 ዓ.ም
የተቀናጀ የኤርፖርትና የድንበር አስተዳደር ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ላይ ያተኮረ የምክክርና የግብዓት ማሰባሰቢያ መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል።
የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል እና የኤርፖርትና ድንበር አስተዳደር ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም ዐቢይ ኮሚቴ ሰብሳቢ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የትራንስፎርሜሽን ፕሮግራሙ የኢትዮጵያን የደኅንነት ስጋቶች አስቀድሞ ለመከላከል፣ የሳይበር ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና በዲጂታል ዘመን ኢትዮጵያ ያላትን ተወዳዳሪነት ለማስቀጠል ወሳኝ ነው።
ፕሮግራሙ ስጋቶችን በመረጃ አስደግፎ ለማወቅና ለመከላከል እንዲሁም በተቋማት መካከል የመረጃ ልውውጥን በማሳደግ ሽብርተኝነት፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች፣ የገንዘብና የመሣሪያ ዝውውርን በጋራ ለመመከት አቅም እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
ፕሮግራሙ ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎች እንዲለሙ በማድረግ የሳይበር ሉዓላዊነትን በማረጋገጥና አሰራሮች በሰው ሰራሽ አስተውሎት (AI) እና በሰለጠነ የሰው ኃይል እንዲደገፉ ግብ የጣለ መሆኑንም አስረድተዋል።

ለዚህም ስኬት የተዘጋጀው ፍኖተ-ካርታ የሚያስፈልጉትን የቴክኖሎጂ አቅም፣ የአሠራር ሥርዓቶች ደረጃ፣ የሰው ሀብት፣ የመሠረተ-ልማት አቅርቦት እንዲሁም የሕግና የቁጥጥር ጉዳዮችን ለይቶ ማስቀመጡን አብራርተዋል።
ፕሮግራሙ የሀገሪቷን የጂኦ-ስትራቴጂክ ቁመና ለማስጠበቅና የበለጸገች ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ አንዱ ማስፈጸሚያ መሣሪያ እንደሆነ ገልጸዋል።
የኢትዮጵያን ጂኦ-ስትራቴጂክ ሉዓላዊነት ለማስጠበቅ የድንበርና የኤርፖርት ደኅንነቶችን ማዘመን እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።
የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት አስተዳደር ምክትል ዋና ዳይሬክተርና የኤርፖርትና ድንበር አስተዳደር ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም የቴክኒክ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዳንኤል ጉታ በበኩላቸው፤ የዲጂታል ዘርፉ ቁልፍ የኢኮኖሚ ምሰሶ መደረጉ በሁሉም ዘርፍ እመርታዊ ውጤት እንዲገኝ እያደረገ ነው ብለዋል።
የተቀናጀ የኤርፖርትና የድንበር አስተዳደር ትራንፎርሜሽን ፕሮግራምም የድንበር አስተዳደርን በማዘመን ውጤታማ ውሳኔዎችን ለማሳለፍ ትልቅ ዕድል እንደሚፈጥር ገልጸዋል።
የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር ጎሳ ደምሴ፤ የሚሰጡ አገልግሎቶች የኢትዮጵያን ብሔራዊ ጥቅም፣ ደኅንነትና ዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃን የጠበቁ መሆን አለባቸው ብለዋል።

በዚህም ተቋማት የአገልግሎት ጥራትና ደኅንነት የሚያረጋግጥ አቅምና አሰራርን በማጎልበት ውጤታማ የአሰራር ሥርዓት መገንባት እንደሚኖርባቸው ተናግረዋል።
በተቀናጀ የኤርፖርትና የድንበር አስተዳደር ትራንስፎርሜሽን ፕሮግራም መሰረት የሚቀረጸውን ፍኖተ ካርታም በሶስት ምዕራፎች ከፋፍሎ ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት እንደሚሰራ መግለጻቸዉን ኢዜአ ዘግቧል፡፡