በዘንድሮው ዓመት የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ከፍ ያለ ውጤት ያመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል- ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

You are currently viewing በዘንድሮው ዓመት የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ከፍ ያለ ውጤት ያመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል- ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር)

AMN- ሰኔ 23/2018 ዓ.ም

በዘንድሮው ዓመት የ12ኛ ክፍል ተፈታኞች ከፍ ያለ ውጤት ያመጣሉ ተብሎ ይጠበቃል ሲሉ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ገለጹ፡፡

የተፈጥሮ ሳይንስ የመጀመሪያ ዙር ተፈታኞች በኦንላይን ፈተና መውሰድ ጀምረዋል።

በፈተና ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) ጨምሮ የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) እንዲሁም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ተገኝተዋል።

በአዲስ አበባ 131 የፈተና ጣቢያወች ያሉ ሲሆን ፈተናው በበይነ መረብ ከሰኔ 23 እስከ ሃምሌ 16 ቀን 2018 ዓ.ም በስድስት ዙር ይሰጣል።

የወረቀት ተፈታኞች ከሃምሌ አንድ ጀምሮ ፈተና መውሰድ እንደሚጀምሩ የተገለጸ ሲሆን ዘንድሮ 563 ሺህ 501 ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ ተመዝግበዋል።

ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በማስጀመርያ መርሐ ግብሩ ላይ ተገኝተው ባስተላለፉት መልእክት፣ ለፈተናው የማጠናከሪያ ትምህርትን ጨምሮ በርካታ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን ተከትሎ በዘንድሮ ዓመት የተሻለ ውጤት ይጠበቃል ብለዋል።

ተማሪዎች በራሳቸው፣ በብቃት በልበ ሙሉነት ተፈትነው ለሀገር ጠቃሚ ዜጋ እንዲሆኑ መልእክት አስተላልፈዋል።

ባለፈው ዓመት 20 በመቶ ብቻ በበይነ መረብ እንደተሰጠ አስታውሰው ዘንድሮ 62 በመቶ በበይነ መረብ ፈተናውን መስጠት እንደተቻለ አንስተዋል፡፡

በቀጣይ ዓመት ሙሉ በሙሉ በበይነ መረብ ለመስጠት መታቀዱም ተገልጿል።

የአዲስ አበባ ከተማ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ እንደ አዲስ አበባ 58 ሺህ 309 ተማሪዎች በ131 የፈተና ጣቢያወች ፈተናውን እንደሚወስዱ ገልፀዋል።

በቤተልሔም አየነው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review