AMN- ሰኔ 23/2018 ዓ.ም
ወጣቱ ትውልድ መዲናችንን ከዲጂታሉ ዘመን የሀሰት መረጃዎች ታድጎ የሰላም ግንባታ ዋልታ ሊሆን ይገባል ሲሉ የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ ገለጹ፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ከአዲስ ሚዲያ ኔትወርክ ጋር በጋራ የሚያዘጋጀው “አውደ-ሰላም” የህዝብ ውይይት የቴሌቪዥን ፕሮግራም፣ “የወጣቶች ሚና ለዘላቂ ሰላም ግንባታ” በሚል ርዕስ በአድዋ ድል መታሰቢያ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የአዲስ አበባ ሰላምና ፀጥታ አስተዳደር ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሊዲያ ግርማ፤ ወጣቱ ትውልድ በአዲስ አበባ ሁለንተናዊ የልማትና የሰላም ጉዞ ውስጥ ያለውን የማይተካ ሚና አብራርተዋል።

አዲስ አበባ የኢትዮጵያ ብቻ ሳትሆን የአፍሪካውያን እና የዓለም አቀፍ ተቋማት መዲና መሆኗን በማንሳት የከተማዋ ሰላም በዋናነት የሚረጋገጠው በወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ነው ብለዋል።
ዛሬ በምንገኝበት የዲጂታል ዘመን፣ ማህበራዊ ሚዲያው ወጣቱን ወደተሳሳተ አቅጣጫ ለመምራት ትልቅ መሳሪያ እየሆነ መጥቷል ያሉት ኃላፊዋ፤ በመሆኑም ወጣቱ እውነትና ሀሰትን በመለየት፣ ስሜታዊነትን በማስወገድ የከተማችን የሰላም ዘብ ሊሆን ይገባል ሲሉም ገልጸዋል፡፡
አክለውም ዛሬ በከተማችን እየተሰሩ ያሉ የኮሪደር ልማቶች እና የስማርት ሲቲ ፕሮጀክቶች የወጣቱ አሻራ ያረፈባቸው መሆናቸውን ጠቅሰው ወጣቱ የሰላም ተጠቃሚ ብቻ ሳይሆን አምባሳደርና ጠባቂ መሆን እንዳለበት አፅንኦት ሰጥተዋል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት ምሁራን ታምሩ ፈይሳ (ዶ/ር) እና ጃራ ሰማ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ወጣቶችን ከሱስና ከተሳሳቱ አመለካከቶች በማራቅ እንዴት በሀገር ግንባታ ላይ የነቃ ተሳትፎ ማድረግ እንደሚቻል የሚዳስስ ጥናታዊ ፅሁፍ አቅርበዋል፡፡
በበረከት ቴዎድሮስ