የከተማ አስተዳደራችንን የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ ማካሄድ ጀምረናል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

You are currently viewing የከተማ አስተዳደራችንን የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ ማካሄድ ጀምረናል- ከንቲባ አዳነች አቤቤ

AMN- ሐምሌ 10/2018 ዓ.ም

የከተማ አስተዳደራችንን የ2018 በጀት ዓመት ማጠቃለያ ስራዎች አፈፃፀም ግምገማ ማካሄድ ጀምረናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ ለሶስት ተከታታይ ቀናት በሚቆየው የአፈፃፀም ግምገማ መድረክ በበጀት ዓመቱ ለመፈፀም ያስቀመጥናቸውን ግቦች እንዲሁም የ2018 በጀት ዓመት የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ እቅዳችን ማጠቃለያ ዓመትም በመሆኑ ከባለፉት 5 ዓመታት አፈፃፀም ጋር አያይዘን የምንገመግም ይሆናል ብለዋል፡፡

እንደሚታወቀው ባለፉት 5 ዓመታት ያቀድናቸውን ስትራቴጂክ ግቦች በተሟላ ሁኔታ ለመተግበር በታማኝነት፣ በቅንነት ያለ እረፍት 24/7 ሰርተን በርካታ ውጤቶችን አስመዝግበናል ሲሉም ገልጸዋል።

በተለይም አዲስ አበባን ከማይጠቅሙ አጀንዳዎች በማውጣት የልማት እና የሰላም ማዕከል እንድትሆን ማድረግ እንደተቻለም አንስተዋል፡፡

እንዲሁም ማህበራዊ ፍትህ የነገሰባት፣ ፅዱ፣ አረንጓዴ፣ ውብ እየሆነች በመምጣቷ የዓለም ትኩረትን ስባለችም ነው ያሉት።

በእርግጥ ከስኬቶቻችን ባሻገር ዛሬም ያልተሻገርናቸው ተግዳሮቶች አሉብንም ብለዋል፡፡

በተለይ የአመራራችን የውጤታማነት ልዩነቶች፣ በከተማችን የሚታዩ የኑሮ ውድነት እና ፍልሰት ችግሮችን በጥልቀት የምንገመግም ይሆናል ሲሉም ገልጸዋል።

በርካታ ስኬቶችን ብናስመዘግብም ከህዝቡ የመልማት ፍላጎት እና ከብልፅግና ግባችን አንፃር ብዙ ስለሚቀረን ስኬቶቻችንን ማስፋት፤ ተግዳሮቶች ደግሞ ለይተን መፍታት በቀጣይ በጀት ዓመት የላቀ ስኬት ማስመዝገብ የግምገማችን ማዕከል ይሆናል ብለዋል፡፡

ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎች ላይ እንወያያለንም ብለዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review