AMN- ሰኔ 23/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ የተገነቡ የስዕብና ማዕከላት ወጣቶች ልምድ የሚለዋወጡባቸው፣ የፈጠራ አቅማቸውን ወደ ሥራ የሚቀይሩባቸው እና በስነ-ምግባር የሚታነጹባቸው ዘመናዊ የልህቀት ማዕከላት እየሆኑ መምጣታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ገለጸ፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ “ስብዕና ልማት ለትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ ሲካሄድ የቆየው የወጣቶች የኪነ-ጥበብና የሥራ ፈጠራ የውድድር የማጠቃለያ መድረክ በአድዋ ድል መታሰቢያ ተካሂዷል።
በመድረኩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አስግደው ኃይለጊዮርጊስ፤ ወጣቶች በከተማዋ የኮሪደር ልማት፣ የስፖርት ማዕከላት ግንባታና በዘመናዊ የኢኮኖሚ መዋቅሮች ውስጥ ያላቸው ተሳትፎ የልማቱ ባለቤትና ተጠቃሚ እያደረጋቸው መሆኑን ተናግረዋል።

የወጣቱ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ተሳትፎ በላቀ ደረጃ መኖሩ ለሀገራችን ብሩህ ተስፋ ዋስትና ነው ያሉት ኃላፊው ፤ ወጣቶች በስሜታዊነት ሳይሆን በዕውቀት እንዲመሩ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በከተማዋ የተገነቡት 114 የወጣት ስዕብና መገንቢያ ማዕከላት ወጣቱ ከጠባብ አስተሳሰብ ወጥቶ ሰፊ ሀገራዊ ራዕይ እንዲኖረው የሚያግዙ የንቃተ-ህሊና እና የክህሎት ማብሰያ መሳሪያዎች እንደሆኑም ተናግረዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ለወጣቶች የገነባቸው የስዕብና ማዕከላት ወጣቶች ልምድ የሚለዋወጡባቸው፣ የፈጠራ አቅማቸውን ወደ ስራ የሚቀይሩባቸው እና በስነ-ምግባር የሚታነጹባቸው ዘመናዊ የልህቀት ማዕከላት እየሆኑ መምጣታቸው በመድረኩ ተመላክቷል።

በዝግጅቱ ላይ ባህላዊ የፈጠራ ስራዎች፣ ውዝዋዜዎችን፣ ዘመናዊ ዳንስን እና የተለያዩ የኪነ-ጥበብ ስራዎች ለውድድር ቀርበዋል። በፈጠራ ውድድሩ ላሸነፉ ተወዳዳሪዎች ሽልማት ተበርክቶላቸዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ወጣቱን በቴክኖሎጂና በስራ ፈጠራ በማስታጠቅ ተወዳዳሪና አሸናፊ ትውልድ ለመፍጠር የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል በመድረኩ ተመላክቷል።
በመሀመድኑር ዓሊ