ታሪካዊ ቅርሶችን ከ”ዕዳ” ወደ “የጋራ በረከት” የመቀየር አዲስ ትርክት ፈጥረናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ታሪካዊ ቅርሶችን ከ”ዕዳ” ወደ “የጋራ በረከት” የመቀየር አዲስ ትርክት ፈጥረናል – ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ሰኔ 24/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ ቀደም ሲል የነበራትን የቱሪስት መስህቦች የታሪክ ኩራት ብቻ ወደ ጎን በመተው፣ ዘርፉን ወደ ላቀ የኢኮኖሚ ምሰሶነትና የጋራ በረከትነት ለመቀየር የሚያስችል ሰፊ የመሠረተ ልማት እና ታሪካዊ ለውጥ እያደረገች መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቱሪስት መስህቦችንና የዘርፉን ሥራዎች በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ፤ ቀደም ባሉት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፉ እንደ አንድ ዋና የኢኮኖሚ ሞተር ሳይሆን እንደ ደጋፊ ይታይ እንደነበር አስታውሰዋል።

ይሁንና አሁን ላይ መንግሥት የፖሊሲ ማሻሻያ በማድረግ ቱሪዝምን ከግብርና፣ ከኢንዱስትሪ፣ ከማዕድንና ከቴክኖሎጂ ጋር በመደመር አምስተኛው ሀገራዊ የኢኮኖሚ ምሰሶ አድርጎ መቅረጹንና ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ጭምር የገበያ ትስስር እንዲፈጥር እየተሠራ መሆኑን ገልጸዋል።

በዘርፉ የታሪክና የትረካ አቀራረብ ችግሮችን በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲያብራሩ፤ ቀደም ሲል የነበረው ትረካ አንዱን አካባቢ ከፍ ለማድረግ ሌላውን ዝቅ የሚያደርግና እርስ በርሱ የሚቃረን በመሆኑ ሳቢያ፣ ዜጎች ቅርሶችን እንደ በረከት ሳይሆን እንደ ዕዳ የሚያዩበትና የባለቤትነት ስሜት የሚያጡበት እንደነበር ጠቁመዋል።

ቅርሶች በየሰፈሩና በየመንደሩ ሰዎችን የሚለያዩ ሳይሆኑ የሁሉም ኢትዮጵያውያን የጋራ ሀብት ሊሆኑ ይገባል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን ላይ ሀገሪቱ ሁሉንም እኩል የሚያቅፍና የሚያኮራ የጋራ ትርክት እየገነባች መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል።

የኢትዮጵያን የቱሪስት መዳረሻዎች የምህንድስና ጥበብና አቅምን በማስረዳት ረገድ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የላሊበላ ውቅር አብያተ ክርስቲያናትን በምሳሌነት አንስተዋል።

ላሊበላ ከተለመደው ከታች ወደ ላይ የመገንባት ሥርዓት ውጪ፣ ከላይ ወደ ታች ተፈልፍሎ የተሠራበት ጥበብ በዓለም ላይ ወደር የሌለው የላቀ የምህንድስና ዕውቀት ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።

በተጨማሪም የሶፍ ዑመር ዋሻ የተፈጥሮን አቀማመጥ ለሰው ልጅ አገልግሎት ማለትም ለስብሰባ፣ ለመማሪያና ለመመገቢያ አዳራሽነት ለማዋል የተጠቀሙበትን ጥበብ የሚያሳይ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከላሊበላና ሰቆጣ እስከ አክሱም የተዘረጉት የድንጋይ ዋሻዎች የጥንት አባቶች አስቸጋሪ የተፈጥሮ መልክዓ ምድርን ወደ መኖሪያነትና መጓጓዣነት የቀየሩበት ታላቅ ታሪክ መሆናቸውን አብራርተዋል።

ኢትዮጵያ ካላት እምቅ የታሪክና የተፈጥሮ ሀብት ተጠቃሚ እንድትሆን ዝም ብሎ ከመኩራት ባለፈ በጀት በመመደብ፣ ዕውቀትን በማቀናጀትና መሠረተ ልማቶችን በማስፋፋት ቅርሶቹን ወደ እውነተኛ የኢኮኖሚ ገቢና የሥራ ዕድል የመቀየር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዘርፉ ለገቢ፣ ለውበት፣ ብሎም የመደመር እሳቤን ለማስረፅና አንድነትን ለማጠናከር ጉልህ ድርሻ እንዳለው አብራርተዋል።

በሚካኤል ህሩይ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review