AMN ሰኔ 18/ 2018 ዓ.ም
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባካሔደው 28ኛ መደበኛ ጉባኤው የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ አጽድቋል።
የሕግና ፍትህ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ እፀገነት መንግስቱ የፌዴራል የሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅን ሪፖርትና የውሳኔ ሀሳብ በዝርዝር አቅርበዋል።
ረቂቅ አዋጁ በኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 34 ንዑስ አንቀጽ (5) መሠረት እንዲሁም አንቀጽ 78 (5) መሠረት የግል እና የቤተሰብ የሕግ ጉዳዮችን አስመልክቶ የሚነሱ አለመግባባቶችን በፈቃደኝነት ላይ በተመሰረተ ሁኔታ በሃይማኖታዊ ሕጐች ለመዳኘት የሚያስችል መሆኑን ገልፀዋል።
ሰብሳቢዋ አክለውም፣ ረቂቅ አዋጁ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች እንደ አንድ የሀገራችን የፍትህ አካል የዳኝነት ነጻነታቸው ተጠብቆና ተጠያቂነት የሰፈነበት አሰራር የሚያሰፍን ቀልጣፋና ተደራሽነት ያለው የዳኝነት አገልግሎት የሚሰጥ መሆኑን አንስተዋል።

ረቂቅ አዋጁ ሃይማኖታዊ እሴቶችን የሚያከብር፣ ከኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ-መንግሥት ጋር የማይቃረን እና ረቂቅ አዋጁ የፍርድ ቤቶቹን ተጠሪነት፣ አደረጃጀት እና የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች አስተዳደር ጉባዔን የሚያቋቁም እንደሆነ ጨምረው አንስተዋል።
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው፣ ረቂቅ አዋጁን ለማዳበር የተዘጋጁት መድረኮች አሳታፊ እንደነበሩ አስተያየት ሰጥተዋል።
በመጨረሻም፣ ምክር ቤቱ በረቂቅ አዋጁ ላይ ሰፊ ውይይት ካደረገ በኋላ፣ የፌዴራል ሸሪዓ ፍርድ ቤቶች ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ፣ አዋጅ ቁጥር 1428/2018 አድርጎ በሙሉ ድምፅ ማጽደቁን ከምክር ቤቱ ያገኘነዉ መረጃ ያመላክታል፡፡