ሕዝብ በባለቤትነት የሚሳተፍበት የሰለጠነ ውይይት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት

You are currently viewing ሕዝብ በባለቤትነት የሚሳተፍበት የሰለጠነ ውይይት ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት

AMN – ሰኔ 26/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያን ስር የሰደዱ ታሪካዊና ፖለቲካዊ ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት፣ ከጠመንጃ ድምፅ ይልቅ የሰለጠነ ውይይትና ምክክር አዋጭና ሁሉንም አሸናፊ የሚያደርግ አማራጭ ነው።

“በውይይት ብቻ የምትጸና ሀገር” የሚለውን እሳቤ እንደ መርህ በማንገብ ወደ ምክክር መግባት ያስፈልጋል።

በየደረጃው የሕዝብ አስተያየትና አጀንዳ በማሰባሰብ ከመጨረሻው ምዕራፍ የደረሰው ሀገራዊ ምክክር፤ ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም፣ ለሰለጠነ ፖለቲካዊ ባህል ግንባታ እና ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ምስረታ ዋስትና የሚሆን ነው።

ምክክሩን ከሌሎች ውይይቶችና ንግግሮች ልዩ የሚያደርገው አንዱና ዋናው ነገር በየደረጃው የሚገኘውን ሕዝብ ከሁሉም የማኅበረሰብ ክፍል ያሳተፈ መሆኑ ነው።

ከዚህ ቀደም በፖለቲካ ተዋናዮች ብቻ ይታጠር የነበረውን አሠራር በማስፋት፣ ሕዝቡም በሀገሩ ጉዳይ ላይ የፍላጎቱንና የድርሻውን የሐሳብ መዋጮ እንዲያጋራ በር የከፈተ ነው።

ሂደቱ ከፖለቲካ ፓርቲዎችና ከታዋቂ ግለሰቦች አልፎ፤ አርሶ አደሩን፣ ወጣቱን፣ ሴቶችን፣ የሃይማኖትና የሀገር ሽማግሌዎችን እንዲሁም ልዩ ትኩረት የሚሹ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ሁሉ በማሳተፍ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሥራው ሲከናወን ቆይቷል።

እያንዳንዱ የማኅበረሰብ ውይይት፣ የአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት እና የአጀንዳ ቀረጻ በየጊዜው ደረጃ በደረጃ ለሕዝብ ይፋ እየተደረገ የተከናወነ መሆኑም የሂደቱን ግልጸኝነት የሚያረጋግጥ ሆኗል።

ሕዝቡ ሐሳቡን የሚያንጸባርቅበት መድረክ መፈጠሩም የምክክሩ ውጤት የጋራ አመኔታን የሚያተርፍ እንዲሆን ያስችላል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን እንዳስታወቀው፣ ሐምሌ 8 በሚጀምረው የመጨረሻው ምዕራፍ የምክክር ጉባኤ ላይ 4 ሺህ ተወካዮች ይሳተፋሉ።

ከእነኚህ ተሳታፊዎች መካከል አንድ ሦስተኛ የሚሆኑት በሀገሪቱ ከሚገኙ 130 ወረዳዎች የተወጣጡ የሕብረተሰብ ክፍሎች መሆናቸው ተገልጿል።

ኮሚሽኑ ተቋቁሞ ወደ ሥራ ከገባበት ጊዜ ጀምሮ አሳታፊነትንና አካታችነትን ግንባር ቀደም መርሆቹ በማድረግ፣ የተለያዩ ተሳታፊዎችን በውክልና ሲያሳትፍ ነው የቆየው።

በአጀንዳ ማሰባሰብ ሂደት ላይ የተሳተፉትን ከየሕብረተሰብ ክፍሉ በማስመረጥ፣ አጀንዳን ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ሲያሰባስብም የብዙ አካላትን ተሳትፎ እና ውክልና እያረጋገጠ ተከናውኗል።

ሂደቱ ሕዝብ ከሚገኝበት መሠረታዊ ወይም ቀዳሚ የሕብረተሰብ ክፍል ጀምሮ፤ በክልል ደረጃ የተዋቀሩ ማኅበራትን፣ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትን፣ የፖለቲካ ፓርቲዎችን እና የሲቪክ ማኅበራትን ያሳተፈም ነው።

ይህም በአንድ ወገን ሳይወሰን ሁሉንም ባለድርሻ አካላት በማካተት አሳታፊነቱን በሂደቱ እውን አድርጓል።

በዚህም የምክክር ሂደቱ ባለቤት ሕዝብ፣ የተለያዩ ማኅበራትና ተቋማት እንዲሆኑ ጠንካራ መሠረት ጥሏል።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review