AMN-ሰኔ 27/2018 ዓ.ም

ለሶስት ወራት የሚቆየው 3ኛው ዙር የ2018 በጀት ዓመት ሀገር አቀፍ የብክለት ቅነሳ ንቅናቄ በይፋ ተጀምሯል።
ፅዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ ብሄራዊ ንቅናቄን ያስጀመሩት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ተመስገን ጥሩነህ የአካባቢ ብክለት ቅነሳ የአካባቢ ጥበቃ ጉዳይ ብቻ እንደማይታይ ይልቁንም ከሀገሪቱ የኢኮኖሚ ምርታማነት እንዲሁም ከሕዝብ ጤና እና የወደፊት እጣ ፋንታ ጋር የተሳሰረ መሆኑን ተናግረዋል።


ኢትዮጵያ በአካባቢ ጥበቃ ስራዎች በአከናወነችው ተግባራት በአፍሪካ ተምሳሌት እንድትሆን እንዳስቻላት ያነሱት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተመዘገቡ ስኬቶችን በማጠናከር መጪው ትውልድ የሚረከባት ኢትዮጵያ ፅዱ ውብ ጤናማና አረንጓዴ ኢትዮጵያ ትሆናለች ሲሉ ተናግረዋል።

የኢፌዴሪ ፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሶስተኛው ዙር ፅዱ ኢትዮጽያ ለትውልድ ሀገራዊ ንቅናቄ በሁለቱ ዙሮች የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከርና በማስፋት ለመጪው ትውልድ ፅዱ ኢትዮጵያን ለማውረስ በቁርጠኝነት ሊሰራ ይገባል ብለዋል።
በአገር አቀፍ ደረጃ ንፁህ፣ ጤናማና ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢን በመፍጠር ኢትዮጵያ የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ እየተከናወኑ ያሉ፤ ፅዱ እና አረንጓዴ አካባቢን
መፍጠር ዓላማ ያደረጉ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ-ግብር፣ የወንዝ ዳርቻ እና የኮሪደር ልማት ፕሮጀክቶች ለከተሞች ጽዳትና ውበትን
ከመፍጠራቸው ባሻገር የአካባቢ ብክለትን በመቀነስ አበረታታች ውጤቶች መመዝገባቸውን አስታውሰዋል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ሌሊሴ ነሜ (ዶ/ር) የዘንድሮው የአካባቢ ብክለት ቅነሳ የፕላስቲክ፣ የአደገኛ ኬሚካልና የድምፅ ብክለቶችን መከላከልና የአካባቢና ማህበረሰብ ተፅዕኖ ግምገማ ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተግባራት ላይ ትኩረት እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
ንቅናቄውን ለማሳካት ከመንግስታዊ ተቋማት ባሻገር ሌሎች የግል ተቋማትም በቁርጠኝነት መሳተፍ እንደሚገባቸው ያነሱት ዋና ዳይሬክተሯ በከተማ ጽዳት ዘመቻ፣ በትምህርት ተቋማት የመሳሰሉ ሁነቶችን በመጠቀም የግንዛቤ መፍጠሪያ ንቅናቄው በርካታ የህብረተሰብ ክፍሎችን ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሰራ አብራርተዋል።
በታምሩ ደምሴ