AMN – ሰኔ 28/2018 ዓ.ም
በ23ኛው የዓለም ዋንጫ ወደ ሩብ ፍፃሜ ለመግባት የሚደረጉ ተጠባቂ ጨዋታዎች ዛሬም ቀጥለው ይከናወናሉ። ብራዚል ከ ኖርዌይ ምሽት 5:00 ሰዓት በኒውዮርክ ኒውጀርሲ ስታዲየም የሚያደርጉት ፍልሚያ ቀዳሚው ጨዋታ ነው።
ብራዚል ከ24 ዓመት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የዓለም ቁንጮ ለመሆን እየጣረች ትገኛለች። በ32ቱ የማጣሪያ ዙር በጃፓን የተፈተነችው የአምስት ጊዜ የዓለም ዋንጫ አሸናፊዋ 2ለ1 በማሸነፍ ነበር ለዛሬው ጨዋታ የበቃችው።
በብራዚል በኩል ቪኒሺየስ ጁኒዮር ፣ ማቴኡስ ኩኝሃ እና ቡርኖ ጉማይሬሽ በዛሬውም ጨዋታ ልዩነት የፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል። ቪኒሺየስ አራት ግብ ሲያስቆጥር ፣ ኩኝሃ ደግሞ ሦስት ግቦች አሉት ፤ በፈጠራ በኩል የተዋጣለት የኒውካስትሉ አማካይ ወደ ግብነት የተቀየሩ አራት ኳሶችን አቀብሏል።

ከ28 ዓመታት በኋላ ወደ ዓለም ዋንጫ ውድድር የተመለሰችው ኖርዌይ ኮትዲቯርን 2ለ1 በመርታት ነበር ወደ 16ቱ ጥሎ ማለፍ የተሸጋገረችው።
በኖርዌይ ጉዞ ውስጥ የአጥቂው ኧርሊንግ ሃላንድ ሚና ጎልቶ ይታያል። የ25 ዓመቱ የማንችስተር ሲቲ አጥቂ በመጀመሪያ የዓለም ዋንጫው አምስት ግቦችን አስመዝግቦ ለከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት እየተፎካከረ ይገኛል። አንቶኒዮ ኑሳ እና አምበሉ ማርቲን ኦዴጋርድ ሌሎች የኖርዌይ የማጥቃት ሃይል ናቸው።
ኖርዌይ በማጥቃቱ ልዩነት ፈጣሪነቷን ብታሳይም በመከላከሉ ረገድ መሻሻል ማሳየት ይጠበቅባታል። በስቴል ሶልባከን የሚመራው ብሔራዊ ቡድን በአራት ጨዋታ ስምንት ግቦች ተቆጥሮባታል።
በዛሬ ጨዋታ በብራዚል በኩል ጉዳት ላይ የነበረው ራፊንሃ ወደ ሜዳ እንደሚመለስ ካርሎ አንቸሎቲ አረጋግጠዋል።
ሁለቱ ሀገራት በዓለም ዋንጫ ሲገናኙ የዛሬው ለሁለተኛ ጊዜ ነው። ከዚህ ቀደም እኤአ 1998 በምድብ ጨዋታ ላይ ተገናኝተው ኖርዌይ 2ለ1 ማሸነፍ ችላ ነበር።
ሜክሲኮ ከ እንግሊዝ

ሌላኛው የዕለቱ ተጠባቂ ጨዋታ የጣምራ አዘጋጇ ሜክሲኮ እንግሊዝን የምትገጥምበት ነው። ሜክሲኮ ከተጠበቀው በላይ ድንቅ ብቃት እያሳየች መጥታለች። ሀገሪቱ እስካሁን ያደረገቻቸውን አራቱንም ጨዋታዎች ምንም ግብ ሳይቆጠርባት አሸንፋለች።
ለሊት 9:00 የሚጀምረው ጨዋታ ታሪክ ጠገብ በሆነው ስታዲዮ አዝቴካ ይከናወናል። ስታዲየሙ ለእንግሊዝ ጥሩ ትዝታ የለውም ፤ ከ40 ዓመት በፊት በ1986ቱ የዓለም ዋንጫ በሩብ ፍፃሜ በአርጀንቲና 2ለ1 የተሸነፉበት ነው።
በወቅቱ ዲያጎ አርማንዶ ማራዶና “የፈጣሪ እጅ” የሚል ስያሜ የሰጣት አሁንም ድረስ አነጋጋሪ የሆነች የእጅ ኳስ ግብ እንዲሁም ስድስት ተጫዋቾችን አልፎ ባሳረፋት ሌላ ኳስ ነበር አርጀንቲና 2ለ1 ማሸነፍ የቻለችው።
ሜክሲኮ በአንፃሩ አዝቴካ የምትመካበት ስታዲየሟ ነው። 10 የዓለም ዋንጫ ጨዋታ አድርጋ ስምንቱን ስታሸንፍ በሁለቱ አቻ ተለያይታለች። ዛሬም ይህን አስደናቂ ታሪኳን ለማስቀጠል ወደ ሜዳ ትገባለች።

በጨዋታው በእንግሊዝ በኩል አምስት ግቦችን ያስቆጠረው ሀሪ ኬን ይጠበቃል። የባየርን ሙኒኩ አጥቂ በ32ቱ የማጣሪያ ዙር በኮንጎ ተፈትነው 2ለ1 ሲያሸንፉ ሁለቱንም ግቦች አስቆጥሮ የቡድኑ የልብ ምት መሆኑን አስመስክሯል።
በሜክሲኮ በኩል አጥቂው ጁሊያን ኩኖኔስ ልዩነት ፈጣሪ ይሆናል ተብሎ ተገምቷል። ተጫዋቹ በአራት ጨዋታ ሦስት ግቦችን አስቆጥሮ አንድ ግብ የሆነ ኳስ ደግሞ አመቻችቶ አቀብሏል።
ሁለቱ ሀገራት የዓለም ዋንጫ ብቸኛ ግንኙነታቸው ከ60 ዓመታት በፊት እኤአ 1966 ላይ ነበር። እንግሊዝ ብቸኛ የዓለም ዋንጫ ባሸነፈችበት በዚያ ዘመን በምድብ ጨዋታ ሜክሲኮን 2ለ0 ማሸነፏ ይታወቃል።
በሸዋንግዛው ግርማ