ባለፉት አምስት ዓመታት በክልሎች መካከል ፍትሐዊ የመሠረተ ልማት ሥርጭት ተረጋግጧል – አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

You are currently viewing ባለፉት አምስት ዓመታት በክልሎች መካከል ፍትሐዊ የመሠረተ ልማት ሥርጭት ተረጋግጧል – አፈ ጉባዔ አገኘሁ ተሻገር

AMN – ሰኔ 29/2018 ዓ.ም

የፌዴሬሽን ምክር ቤት 6ኛ የፓርላማ ዘመን፣ 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን አካሂዷል።

ምክር ቤቱ በጉባኤው በሥሩ የሚገኙ የተለያዩ ቋሚ ኮሚቴዎችን የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ሪፖርት ገምግሟል፡፡ በዕለቱ ሪፖርታቸው ከተገመገሙት መካከል የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ አንዱ ነው፡፡

የምክር ቤቱ አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር በበጀት ድጎማና በጋራ ገቢ ሥርጭት ረገድ መሠረታዊ ለውጥ መመዝገቡንና ይህም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስታውቀዋል።

አፈ ጉባኤው አክለውም ባለፉት አምስት ዓመታት ምንም ዓይነት አዲስ የመሠረተ ልማት ሥርጭት ኢ-ፍትሐዊነት እንዳልተከሰተ ገልጸው፣ ወደ ኋላ የቀሩ ጉድለቶችን ለማስተካከልና ክፍተቶችን ለመሙላት ሰፊና ተስፋ ሰጪ ሥራዎች እየተሠሩ መሆኑን ጠቁመዋል።

የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ ሽመልስ አብዲሳ በበኩላቸው፣ በክልሎች ፍትሐዊ ልማትን ለማስፈን ቀደም ሲል የነበሩ ክፍተቶችን የሚቀርፉ አዳዲስ አሠራሮች መዘርጋታቸውን ጠቁመዋል።

ይህንኑ ፍትሐዊነት በስምንት የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች በኩል በቅርበት የመከታተልና የማረጋገጥ ውጤታማ ሥራ መሠራቱንም አክለው ገልጸዋል።

የድጎማ በጀትና የጋራ ገቢዎች ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ ሪፖርትን የኮሚቴው ጸሐፊ አቶ ኃይሉ ኢፋ ለጉባኤው አቅርበዋል።

ጸሐፊው በሪፖርታቸው እንዳመለከቱት፣ በበጀት ዓመቱ ለክልሎች ከተመደበው 314 ቢሊዮን ብር የድጎማ በጀት ውስጥ 304 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብሩ በተሳካ ሁኔታ የተላለፈ ሲሆን፣ ይህ የተላለፈው የድጎማ በጀትም በክልሎች መካከል የመሠረተ ልማት ፍትሐዊነትና ተደራሽነትን ለማረጋገጥ ጠንካራ መሠረት የጣለ ነው።

ምክር ቤቱ የቀረበውን ሪፖርት ከመረመረ በኋላ በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል።

በፈቃዱ መለሰ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review