ኢትዮጵያ የመድሃኒት ምርት አቅሟን ወደ 45 በመቶ አሳድጋለች- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing ኢትዮጵያ የመድሃኒት ምርት አቅሟን ወደ 45 በመቶ አሳድጋለች- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN- ሰኔ 30/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ፣ በጤናው ዘርፍ በመድሃኒት አቅርቦት እና በህክምና ተቋማት ግንባታ መጠነ ሰፊ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የመድሃኒት ምርት አቅሟ ከነበረበት 4 በመቶ ወደ 45 በመቶ ማሳደጓን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ሀገሪቱ በዓለም የመድሃኒት ምርት ኤጀንሲ “ማቹሪቲ ሌቭል ሶስት” ላይ መድረሷንና ይህ ለውጥም በሀገር ውስጥ የሚመረቱ መድሃኒቶች ለኤክስፖርት ደረጃ ተቀባይነት እንዲኖራቸው ማስቻሉን አስታውቀዋል፡፡

የህክምና ፍላጎትን ለማሟላት አዲስ አበባን ጨምሮ በየአካባቢው ሆስፒታሎችን የመገንባትና የማስፋፋት ሥራ እየተከናወነ መሆኑን የጠቀሱ ሲሆን፣ የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ተጨማሪ 1 ሺህ አልጋዎችን በመጨመር አቅሙ እንዲያድግ መደረጉን በማሳያነት አንስተዋል፡፡

ከ14 ሚሊየን በላይ አጎበር በነጻ መሰራጨቱን እና በ58 ወረዳዎች ለመጀመሪያ ጊዜ የክትባት ሥራዎች መጀመራቸውንም ጠቅሰዋል፡፡

በተጨማሪም መንግስት ዘንድሮ ለህክምና መሳሪያዎች ግዢ ከ60 ቢሊየን ብር በላይ፣ ለተለያዩ መድሃኒቶች ደግሞ 70 ቢሊየን ብር ማውጣቱን የገለጹት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የጤና ተቋማትን የማዘመንና የመድሃኒት አቅርቦትን በሀገር ውስጥ የመተካት ሥራ በቁርጠኝነት እየተከናወነ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

በሚቀጥሉት አምስት ዓመታትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆኑና የተሟሉ የህክምና ማዕከላትን መገንባት ዋነኛ ትኩረት እንደሚሆን ተጠቁሟል፡፡

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review