የ17 ዓመቱን የውጭ ንግድ ገቢ በአንድ ዓመት ማሳካት ተችሏል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

You are currently viewing የ17 ዓመቱን የውጭ ንግድ ገቢ በአንድ ዓመት ማሳካት ተችሏል- ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)

AMN – ሐምሌ 1/2018 ዓ.ም

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መደበኛ ጉባዔ ላይ በሰጡት ማብራሪያ፣ ሀገሪቱ ላለፉት 17 ዓመታት ያስመዘገበችውን የ11 ቢሊዮን ዶላር የውጪ ንግድ ገቢ፣ በዘንድሮው በጀት ዓመት ብቻ ማሳካት መቻሉን ገልጸዋል።

ይህ ስኬት ሀገሪቱ በዘንድሮው ዓመት ያቀደችውን የ10.3 በመቶ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማሳካት ቁልፍ ሚና እንደሚጫወት ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ በውጭ ንግድ ዘርፍ 9.4 ቢሊዮን ዶላር ለመሰብሰብ ታቅዶ የነበረ ቢሆንም፣ በተገኘው የላቀ ውጤት 11 ቢሊዮን ዶላር መመዝገቡን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አብራርተዋል።

ከዚህ ገቢ ውስጥ ከወርቅ 5.5 ቢሊዮን ዶላር፣ ከቡና 3.1 ቢሊዮን ዶላር እንደተገኘ ገልፀው፤ ዘንድሮ ኢትዮጵያ በዓለም የቡና ኤክስፖርት 3ኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያ አጠቃላይ የውጭ ካፒታል ፍሰት 38 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የገለጹ ሲሆን፣ አገልግሎት ዘርፍ 9.5 ቢሊዮን ዶላር፣ የሐዋላ (ሬሚታንስ) 7.9 ቢሊዮን ዶላር፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 4 ቢሊዮን ዶላር፣ የውጭ እርዳታና ብድር 5 ቢሊዮን ዶላር ድርሻ እንዳላቸው አመልክተዋል፡፡

ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው የዋጋ ንረትን ለመቆጣጠር እና የግል ዘርፉን በማበረታታት መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት ማስቻሉንም አንስተዋል።

በተለይም ግብርናን በቴክኖሎጂ ማዘመንና ቱሪዝምን ማስፋፋት የውጭ ምንዛሬን ለማሳደግ ጉልህ ድርሻ እንደነበራቸው አብራርተዋል።

በደንብ የተመራ ሪፎርም ማካሄድ በመቻሉ ኢኮኖሚው ከነበረበት ችግር ለመላቀቅ ዕድል አግኝቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህ ውጤት የኢትዮጵያን የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋት ያረጋገጠ እና አህጉራዊ ተወዳዳሪነቷን ያሳደገ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ያካሄደችው ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ሪፎርም፣ የዓለም አቀፍ ጫናዎችን የመቋቋም አቅሟን ከመገንባቱም በላይ እንቅፋቶችን ወደ ዕድል በመቀየር ብሔራዊ ጥቅሟን ማስከበር መቻሏን በተግባር ያሳየ ስኬት እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራርያቸው አመላክተዋል።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review