አዲስ አበባ – የዓለም አቀፍ ስፖርት ቱሪዝም አዲስ መዳረሻ

You are currently viewing አዲስ አበባ – የዓለም አቀፍ ስፖርት ቱሪዝም አዲስ መዳረሻ

AMN – ሚያዝያ 11/2018 ዓ.ም

“ትናንት ኢትዮጵያ ያስተናገደችው የሩጫ ውድድር ከሩጫ በላይ ትልቅ ክስተት ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ሁንዴ ከበደ ገለፁ፡፡

አዲስ አበባ እንዲህ ያለ ዓለም አቀፍ የአትሌቲክስ ውድድር ስታዘጋጅ ይህ የመጀመሪያዋ በመሆኑ፣ ለከተማዋ ታሪካዊ ጅማሮ ነው፡፡

ይህ ኩነት በተለይ ደግሞ አሁን ላይ የከተማ አስተዳደሩ ለስፖርት ቱሪዝም የሰጠውን ከፍተኛ ትኩረት ማሳያ ነው ሲሉ አቶ ሁንዴ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልፀዋል ፡፡

ባለፉት የለውጥ ዓመታት አዲስ አበባ ከተማ የስፖርት ዘርፉን ለማጠናከር ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ አውጥታ ተግባራዊ አድርጋለች ያሉት ኮሚሽነሩ ትናንት የታየው ውድድርም ይህን ኢንቨስትመንት የሚመጥን እና የከተማችንን የእድገት ደረጃ ለዓለም በጉልህ የሚያሳይ ነበር ብለዋል፡፡

ስለሆነም እንደነዚህ ያሉ ታላላቅ የስፖርት ኩነቶች የቱሪዝም ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት ረገድ ሚናቸው እጅግ ከፍተኛ ነው፡፡

በትናንቱ ውድድር ላይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ዝና ያላቸው አትሌቶች ተሳትፈዋል። እንደነ ጋቢ ቶማስ ያሉ ተጽዕኖ ፈጣሪ አትሌቶች እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ተከታዮች ያሏቸው እንግዶች ስለ ከተማችን ያላቸውን መልካም ቆይታ ሲያጋሩ እንደነበር አቶ ሁንዴ ተናግረዋል፡፡

በዚህ ሁነት በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አውጥተን እንኳን ልናገኘው የማንችለው ትልቅ የፕሮሞሽን ሥራ ተሰርቷል እንዲሁም ውድድሩ በቀጥታ ለዓለም መተላለፉም የሀገራችንን ገጽታ ለመገንባት ትልቅ ዕድል ፈጥሯል ነው ያሉት ፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት በመዲናችን የተሠሩት ግዙፍ የልማት ሥራዎች እና የመሠረተ ልማት ግንባታዎች እንዲህ ያሉ ዓለም አቀፍ ኩነቶችን ለማሰናዳት ማገዛቸውን እና እንደ ኮንፈረንስ ቱሪዝም ሁሉ በስፖርት ቱሪዝምም ውጤታማ መሆን የተቻለው ለዘርፉ በተሰጠው ትኩረት እና በተሰራው ስራ መሆኑን አቶ ሁንዴ ገልፀዋል ፡፡

የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ከሌሎች አካላት ጋር በመሆን ከተማዋን ለዓለም የማስተዋወቅ ሥራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል ኮሚሽነር አቶ ሁንዴ ከበደ ከኤ ኤም ኤን ዲጂታል ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡

በያለው ጌታነህ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review