AMN ሐምሌ 7/2018

ለክረምት ዝናብ መፈጠር ምቹ ሁኔታ የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገፅታዎች በሚቀጥሉት ቀናት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
ኢንስቲትዩቱ ለኤኤምኤን በላከው መግለጫ፣ ከሐምሌ 4 እስከ ሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም. የሚኖረው የአየር ሁኔታ፣ ለክረምት ዝናብ ምቹ ሁኔታን የሚፈጥሩ የሚቲዎሮሎጂ ገጽታዎች ይበልጥ እየተስፋፉና እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ አስታውቋል።
በዚህም በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን፣ በመካከለኛው እና በምሥራቅ የሀገሪቷ ክፍሎች ላይ የተሻለ የዝናብ መጠንና ሥርጭት እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።
በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች በአብዛኛው ቦታዎች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙም ትንበያው አመላክቷል።
እንዲሁም የመካከለኛው፣ የሰሜን ምሥራቅና የምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው አሀዛዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩ ተገልጿል።
የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ አካባቢዎች በሚቀጥሉት ቀናት አብዛኛውን ቦታዎች የሚሸፍን ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው ይጠበቃል።
በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብ፣ በሰሜን ምዕራብ፣ በሰሜን ምሥራቅና በመካከለኛው የሀገሪቱ አካባቢዎች ላይ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖርም ተመላክቷል።
በሚቀጥሉት ቀናት በደቡብ ምዕራብ፣ በምዕራብና በሰሜን ምዕራብ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው እርጥበት እንደሚኖራቸው ተመላክቷል።
በመካከለኛው፣ በሰሜን ምሥራቅና በምሥራቅ የሀገሪቱ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው የአፈር ውስጥ እርጥበት እንደሚጠበቅም ተገልጿል።
በመሆኑም የሚኖሩ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀምና የሚጠበቁ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ፣ ቦታ ተኮር የግብርና ሚቲዎሮሎጂ ምክረ ሀሳቦችን ከወዲሁ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።
በሚቀጥሉት ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ በሆኑ የሀገሪቱ ተፋሰሶች ላይ ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው የገጸ ምድር የውኃ ፍሰት እንደሚኖርም ይጠበቃል።
በመሆኑም የሚኖሩ መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀምና የሚጠበቁ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ለመቀነስ፣ ቦታ ተኮር የውኃ ተኮር ሚቲዎሮሎጂ ምክረ ሀሳቦችን ከወዲሁ ተግባራዊ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ተመላክቷል።