AMN — ሐምሌ 11/2018 ዓ.ም

ባለፉት አምስት ዓመታት ደረጃቸውን የጠበቁ ከ20 ሺህ በላይ ሼዶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች መተላለፋቸዉን እና ከ2 ነጥብ 2 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎች ቋሚ የሥራ ዕድል መፈጠሩን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመሥሪያ ቦታዎች ልማት ኤጀንሲ አስታወቀ።
የኤጀንሲዉ ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ አይዳ አወል ለኤ ኤም ኤን እንደገለጹት በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ብቻ ከ373 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚ የሥራ ዕድል ተመቻችቷል።

ከተማ አስተዳደሩ የሥራ ዕድል ፈጠራን በስፋት ለማሳለጥ ምቹ ሁኔታዎችን ከመፍጠር ባለፈ የመሥሪያ ቦታዎችን የማመቻቸት፣ የብድር አገልግሎት የማቅረብና ኢንተርፕራይዞችን በማደራጀት ረገድ ከፍተኛ ትኩረት ሰጥቶ እየሠራ እንደሚገኝም ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።
በዚህም መሠረት ባለፉት አምስት ዓመታት ደረጃቸውን የጠበቁና እንደ ውኃ፣ መብራትና መንገድ ያሉ መሠረተ ልማቶች የተሟሉላቸው ከ20 ሺህ በላይ ሼዶች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች ተላልፈዋል።

በቅርቡ ተመርቆ አገልግሎት መስጠት የጀመረው የገላን ዘመናዊ የኢንዱስትሪ መንደርም ኢንተርፕራይዞች የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመተካት ባለፈ ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ መላክ እንዲችሉ ታስቦ የተገነባ ትልቅ ማሳያ መሆኑን ገልጸዋል።
ከከተማዋ የኮሪደር ልማት ጋር ተያይዞ ቀደም ሲል የነበሩ የከተማዋን ስታንዳርድ የማይመጥኑና ለአደጋ ተጋላጭ የነበሩ ቦታዎችን በመቀየር ረገድም ሰፊ ሥራ መከናወኑን ዋና ዳይሬክተሯ አብራርተዋል።
በዚህም በመንግሥት፣ በባለሀብቶችና በኅብረተሰቡ ተሳትፎ ከ5 ሺህ 500 በላይ ዘመናዊ ሱቆች ተገንብተው ለተጠቃሚዎች የተላለፉ ሲሆን፤ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት ደግሞ ከ91 ሺህ በላይ የሕንጻዎችና የጂ ፕላስ ፎር (G+4) የማምረቻ ቦታዎች ተገንብተው በዕጣና በግልጽነት ለአገልግሎት በቅተዋል።
ኤጀንሲው አሁን ላይ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸሙን እየገመገመ እንደሚገኝና በቀጣይም ለአምራች ኢንዱስትሪው ዘርፍ ልዩ ትኩረት በመስጠት የመሬትና የሼድ አቅርቦትን የማጠናከር ሥራ በትኩረት እንደሚመራ አስታውቋል።
በወርቅነህ አብዮ