አዲስ ዓመት የዘመን መቀየር ብቻ አይደለም፤ የአስተሳሰብ መታደስ፣ የአዲስ ተስፋ መሰነቅና የጋራ ጉዞ አዲስ ምዕራፍ መክፈት ነው- አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

AMN- ጳጉሜን 5/2018 ዓ.ም

አዲስ ዓመት የዘመን መቀየር ብቻ አይደለም፤ የአስተሳሰብ መታደስ፣ የአዲስ ተስፋ መሰነቅና የጋራ ጉዞ አዲስ ምዕራፍ መክፈት ሲሉ የኢፌዲሪ ፌደሬሽን ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸውም፤ በቅድሚያ ለሁሉም የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣ እንኳን ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሰላም፣ በጤናና በደስታ አደረሳችሁ፤ አደረሰን ብለዋል፡፡

አዲሱ ዓመት ከጨለማ ወደ ብርሃን፣ ከግጭት ወደ ሰላም፣ ከውይይት ወደ መግባባት፣ ከልዩነት ወደ አንድነት፣ ከችግር ወደ መፍትሔ፣ ከጉስቁልና ወደ ብልጽግና የምንሻገርበት ዘመን እንዲሆንልን በራሴና በፌዴሬሽን ምክር ቤት ስም ከልብ እመኛለሁ ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አሮጌ ዓመት ሲያልፍ አዲስ ዓመት ይተካል፤ ይህ የተፈጥሮ ዑደት ሰዎች ካለፈው ትናንት እንዲማሩ፣ ነገን በተስፋ ለመገንባት አዲስ ጉዞ እንዲጀምሩ አብነት ይሆናል ብለዋል፡፡

ስለዚህ አዲስ ዓመት የዘመን መቀየር ብቻ አይደለም፤ የአስተሳሰብ መታደስ፣ የአዲስ ተስፋ መሰነቅና የጋራ ጉዞ አዲስ ምዕራፍ መክፈት መሆኑንም አንስተዋል፡፡

ኢትዮጵያ በብዝኀ ቋንቋዎች፣ ማንነቶች፣ ባህሎችና እሴቶች ያሸበረቀች አገር ናት ያሉት አፈ ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር፤ ይህ ብዝኃ ማንነታችን የመለያያ ግንብ ሳይሆን፣ የጋራ ውበታችን፣ የጋራ ሀብታችንና የጋራ መለያችን ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

አበቦች በቀለማቸው ይለያያሉ፤ ውበታቸው የሚገለጠው ግን አብረው ሲያብቡና ተደጋግፈው ሲኖሩ መሆኑን በመግለጽ የኢትዮጵያ ሕዝቦችም በቋንቋቸው፣ በባህላቸውና በማንነታቸው ልዩ ልዩ ሆነው ሳለ፣ በመከባበርና በመደጋገፍ ሲኖሩ፣ ለጋራ ዓላማ በአብሮነት ሲቆሙ ግን የአንድነትን ውብ ምስል ይፈጥራሉ፤ ኃይላቸውንም ያጠነክራሉ ብለዋል፡፡

አሮጌው ዘመን አብቅቶ አዲስ ዘመን ሲተካ “የጎመን ምንቸት ውጣ፣ የገንፎ ምንቸት ግባ” በሚል የተሻለን ነገ ይታለማል፤ ቀጣይ ተስፋም ይሰነቃል፤ በመሆኑም መጪው ዓመት የልዩነት ትርክት የሚደርቅበት፣ ኀብረ ብሔራዊ አንድነታችን የሚጸናበት፣ በአዲስ ወኔና ተስፋ ወደላቀ ልዕልና የምንሻገርበት ዓመት እንዲሆን ተመኝተዋል፡፡

የፌዴሬሽን ምክር ቤትም ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ ባካሄደው ተቋማዊ ሪፎርም በሕገ መንግሥቱ የተጣለበትን ተግባርና ኃላፊነት በላቀ ደረጃ ለመወጣት እየሠራ መሆኑን ስንገልፅ በታላቅ አክብሮት ነው ብለዋል፡፡

ምክር ቤቱ ባለፉት ዓመታት በሕዝቦች እኩልነትና መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተ ኅብረብሔራዊ አንድነት ስር እንዲሰድና የርስ በርስ ግንኙነቱ እንዲጎለብት ያላሠለሰ ጥረት ሲያደርግ መቆየቱን በማንሳት በቀጣዩ የምክር ቤት ዘመንም የበለጠ ትኩረት ሰጥቶ ይሠራልም ነው ያሉት፡፡

በተጨማሪም ምክር ቤቱ የቀረቡለትን የሕገ መንግሥት ትርጉም ውሳኔዎችን በመመርመርና በመወሰን ዜጎች ፍትሕ የማግኘት መብታቸው እንዳይጣበብና በሀገራችን ያለው የሕግ የበላይነት መሠረት እንዲይዝ ሰፋፊ ሥራዎችን ይሰራል ማለታቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመላክታል፡፡

አፈ-ጉባኤ አገኘሁ ተሻገር አክለውም፤ ባለፉት ዓመታት ምክር ቤቱ በሀገር ውስጥና በውጭ ግንኙነት ዘርፍ በተሻለ ደረጃ በመሥራት ሀገራዊ፣ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶችን፣ ትብብሮችንና አጋርነቶችን ማጠናከር ችሏል ብለዋል፡፡

የሚያከናውናቸውን ተግባራት፣ የሚያካሂዳቸውን ውይይቶች፣ የሚወስናቸውን ውሳኔዎች የተለያዩ የመገናኛ ዘዴዎችን በመጠቀም በግልጽ ለሕዝብ ተደራሽ እንዲሆኑ አድርጓል ሲሉም ገልጸዋል፡፡

በሕገ መንግሥቱ በተሰጠው ሥልጣንና ኃላፊነት መሠረት የክልሎችና የፌዴራሉ መንግሥት የጋራ ተብለው የተመደቡ ገቢዎች የሚከፋፈሉበትን፣ እንዲሁም የፌዴራሉ መንግሥት ለክልሎች ድጎማ የሚሰጥበትን ቀመር ሲወስን የቆየ ሲሆን በክልሎች መካከል የተመጣጠነ እድገት እንዲኖር የፌዴራል ድጎማዎች ግልጽነት፤ ተጠያቂነትና ዘላቂነት ባለው መልኩ በፍትሐዊነት ለክልሎች የሚከፋፈልበት የአሠራር ሥርዓት በማሻሻል በርካታ ተግባራት አከናውኗል ብለዋል፡፡

በአጠቃላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በአዲሱ ዓመት ካለፉት ዓመታት ተሞክሮዎችን በመውሰድ የላቀ አፈጻጸም ለማስመዝገብ ያለውን ዝግጁነት እየገለጽኩ አዲሱ ዓመት ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም፣ የፍቅር፣ የመቻቻል፣ የአንድነትና የብልጽግና ዘመን እንዲሆንላችሁ ከልብ እመኛለሁ ሲሉም ገልጸዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review