የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

AMN- ጳጉሜን 5/2018 ዓ.ም

የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ለአዲስ ዓመት የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።

በመልእክታቸውም፤ በቅድሚያ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች፣ ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊታችን አመራሮች፣ መኮንኖች፣ ወታደሮች እና ሲቪል ሠራተኞች እንኳን ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ አደረሰን ብለዋል፡፡

2018 ዓ.ም በርካታ ፈተናዎችን የተጋፈጥንበት፣ በተመሳሳይም የማድረግ አቅማችንና ተልዕኮን የመወጣት ብቃታችንን በተግባር ያረጋገጥንበት ዓመት ነበር ሲሉ ገልጸዋል፡፡

ሠራዊታችን በዓመቱ ያስቀመጥናቸውን ግቦችና ዕቅዶች በተቀናጀና በተጠናከረ አሠራር በማሳካት የተሰጠውን ኃላፊነት በታላቅ ብቃት መወጣቱንም አንስተዋል፡፡

ይህ ውጤት የአንድ አካል ወይም የጥቂት ሰዎች ጥረት ውጤት አይደለም ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤በየደረጃችሁና በየሙያችሁ በትጋት የሠራችሁ፣ የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት ለመጠበቅ በየቦታውና በየሁኔታው የደከማችሁ አመራሮች፣ መኮንኖች፣ ወታደሮችና ሲቪል ሠራተኞች ያደረጋችሁት የጋራ ጥረት የውጤቱ መሠረት ነው። ለዚህም ሁላችሁም ከፍተኛ ምስጋናና አድናቆት ይገባችኋል ብለዋል፡፡

በ2018 ዓ.ም ዋና ትኩረታችን የሀገራችንን ሰላምና ደህንነት ማስጠበቅ፣ ህዝባችንን መጠበቅና የሀገራችንን የልማት ጉዞ ሊያስተጓጉሉ የሚችሉ ሁኔታዎችን መከላከል ነበርም ነው ያሉት፡፡

በዚህም የሰላምና የደህንነት ስጋቶችን በመመከት፣ በተለያዩ አካባቢዎች መረጋጋትን በማስፈንና ህዝቡ ወደ መደበኛ ኑሮው እንዲመለስ በማስቻል ተጨባጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

ይሁን እንጂ ዘላቂ ሰላም በወታደራዊ አቅም ብቻ የሚረጋገጥ ባለመሆኑ ግጭትን የሚያባብሱ ምክንያቶችን መለየት፣ ህዝቡ የሰላምን ጥቅም እንዲገነዘብ ማድረግና ለሰላም የሚያበረክተውን ሚና ማጠናከር እንደሚያስፈልግም አንስተዋል፡፡

ዋና ዓላማችን ሀገር በሰላም እንድትኖር፣ ህዝባችን በሰላም እንዲሠራና እንዲያድግ፣ የልማት ጉዞውም ያለምንም እንቅፋት እንዲቀጥል ማስቻል ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

2018 ዓ.ም የሠራዊቱን የወቅቱን ተልዕኮ በመወጣት ብቻ ያለፈ ዓመት አልነበረም ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ለወደፊቱ የሀገር መከላከያ አቅም ግንባታም ጠንካራ መሠረት ተጥሏል ብለዋል፡፡

ሠራዊቱን ከዘመኑ ጋር ማዘመን፣ ከአናሎግ አሠራር ወደ ዲጂታል አሠራር መሸጋገር፣ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን መጠቀም፣ የሰው ኃይል፣ የሥልጠናና የመሠረተ ልማት አቅምን ማጠናከር ተቀዳሚ ተግባራት እንደነበሩም ገልጸዋል፡፡

በተጨማሪም የመከላከያ አቅምን ለማሳደግ፣ የመከላከያ ኢንዱስትሪን ማጠናከርና በሀገር ውስጥ የመከላከያ ቁሳቁሶችና ቴክኖሎጂዎችን ማምረት የሚያስችል አቅም ለመገንባት ሰፊ ሥራ ተሠርቷል ብለዋል።

ይህም ለሀገራችን የወደፊት የመከላከያ አቅም ግንባታ ወሳኝ መሠረት የጣለ መሆኑን በመግለጽ የሠራዊቱን የሰው ኃይል ብቃት ማሳደግም የ2018 ዓ.ም ትኩረት ነበር ነው ያሉት።

በሥልጠና፣ በሙያ ብቃት፣ በአመራር ልማትና በዘመናዊ አሠራር ላይ በተደረገው ማሻሻያ የሠራዊቱ የማድረግ አቅም ተጠናክሯል፤ የምድርና የአየር ኃይል አቅም ማሳደግና በተቀናጀ መልኩ እንዲሠሩ መደረጉም ለወደፊት የተልዕኮ ዝግጁነታችንን የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡

በ2019 ዓ.ም ሁለት ዋና ትኩረቶች ይኖሩናል፤ የመጀመሪያው የሀገራችንን ሰላም፣ ደህንነትና ሉዓላዊነት ማስጠበቅ ነው ሲሉም ገልጸዋል።

ሁለተኛው ደግሞ ለወደፊቱ የሀገራችንን የመከላከያ አቅም በተሻለ ደረጃ ማዘጋጀትና የሠራዊቱን የማድረግ አቅም ማሳደግ ነው ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ ስለሆነም የተጀመሩትን የሠራዊት ማዘመንና የአቅም ግንባታ ሥራዎች እናጠናክራለን ብለዋል።

በቴክኖሎጂ፣ በሥልጠና፣ በሰው ኃይል፣ በአመራር፣ በመሠረተ ልማትና በመከላከያ ኢንዱስትሪ የተጀመሩትን ሥራዎች ወደተሻለ ደረጃ ለማሸጋገር እንደሚሰራም ጠቁመዋል፡፡

የሠራዊታችን ዝግጁነትም በዘመናዊ አሠራር፣ በተቀናጀ አመራርና በብቁ የሰው ኃይል ላይ ይመሠረታል በማለት በ2019 ዓ.ም የሚጠብቀንን ተልዕኮ በጋራ ትጋት፣ በተቀናጀ አመራርና በጠንካራ የቡድን ሥራ እንወጣዋለን ብለዋል፡፡

መላው ህዝባችን ሰላም እንዲረጋገጥ፣ እንዲሠራ፣ እንዲማርና እንዲያድግ፣ የተሻለ ሀገር እንዲገነባ ይፈልጋል ያሉት ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፤ይህንን የህዝባችንን ፍላጎት ለማሳካት ሠራዊታችን የተሰጠውን ሀላፊነት በሙሉ ቁርጠኝነት ለመወጣት ዝግጁ ነው ሲሉም ገልጸዋል፡፡

ሀገር ሰላም ስትሆን ህዝብ ይሠራል፤ ልማት ይፋጠናል፤ የተሻለ ነገርም ይገነባል። ስለዚህ የ2018 ዓ.ም ስኬታችን የ2019 ዓ.ም ዝግጁነታችንን ያጠናክራልም ብለዋል።

ያለፈውን ልምድ በመጠቀም፣ የተገነባውን አቅም በማጠናከርና የተጀመሩትን ሥራዎች በማስፋፋት ለሚጠብቀን ተልዕኮ ዝግጁ ነን፤ 2019 ዓ.ም የሠራዊታችን አቅም የሚጠናከርበት፣ ዝግጁነቱ የሚያድግበትና ለሀገርና ህዝብ ተጨማሪ ውጤት የሚመዘገብበት ዓመት እንደሚሆንም ገልጸዋል፡፡

ለመላው የሀገራችን ህዝብ በ2018 ዓ.ም ላሳያችሁት ቁርጠኝነት፣ ለሰራዊታችን ላበረከታችሁት የላቀ አስተዋፅኦ ሁላችሁንም ከልብ አመሰግናለሁ፤ የሠራዊቱ ውጤት የህዝባችን ውጤት ነው፤ ለሀገር ሰላምና ደህንነት የምታደርጉት ጥረትም የሀገር አቅም ነው ብለዋል።

በድጋሚ ለመላው የሀገራችን ህዝቦች፣ ለጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችን አመራሮች፣ መኮንኖች፣ ወታደሮችና ሲቪል ሠራተኞች እንኳን ለ2019 ዓ.ም አዲስ ዓመት በሰላም አደረሳችሁ! አዲሱ ዓመት ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም፣ ለህዝባችን ደህንነትና ብልፅግና፣ ለሰራዊታችን የበለጠ አቅም፣ ዝግጁነትና ስኬት የሚያመጣ ዓመት ይሁንልን ሲሉም ገልጸዋል፡፡

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review