AMN- ሐምሌ 13/2018 ዓ.ም
በአቶ አደም ፋራህ የተመራ የፓርቲው የዋናው ጽህፈት ቤት እና የክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች አመራሮች በአዲስ አበባ ከተማ እየተከናወነ ያለውን የተቋማት ግንባታ ስራዎችን ተመልክቷል።
በዚህ ወቅት የብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ አዲስ አበባ የማያቋርጥ ዕድገት ማሳያ ናት ሲሉ ገልጸዋል።
አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለሌሎች የሀገራችን ክልሎች እና ከተማ አስተዳደሮች ትምህርት የሚወስድበት ስራዎችን እያከናወነች ነው፣ በፓርቲ ስራዎችም በተመሳሳይ ምሳሌ የሚሆን ተግባራት እያከናወነ እንደሆነ አንስተዋል።
አዲስ አበባ ከተማ የብልጽግና ፓርቲ እሳቤዎችን እና ኢኒሼቲቮችን በተሟላ መልኩ እየፈጸመች መሆኑን ብዙ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ማሳያዎች አሉ ብለዋል።
ሕዝቡን አስተባብሮ በላቀ ትጋት እና ቁርጠኝነት መስራት በመቻሉ ባለፉት አምስት ዓመታት ስኬት ተግኝቷል።

አዲስ አበባ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር የሚያሸጋግሩ ስራዎችን በመስራት ረገድ የድርሻውን እየተወጣች ነው ያሉት ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ አደም ለዚህም አመራሩ እና ሕዝቡ ምስጋና ይገባዋል ብለዋል።
በብልፅግና ፓርቲ የአዲስ አበባ ቅ/ፅ/ቤት ኃላፊ አቶ ሞገስ ባልቻ በበኩላቸው፣ ሕዝብ በምርጫ የሰጠንን አደራ ለመወጣት፣ የሕዝቡን አዳዲስ የዕድገት ፍላጎት ማዕከል ያደረጉ ስራዎችን መስራት እንደሚገባ አንስተዋል።
የተቋም ግንባታ ለሀገረ መንግስት ከፍተኛ አበርክቶ ያለው በመሆኑ በትኩረት እየሰራን ነውም ብለዋል።
የመንግስት እና የፓርቲ ስራዎችን በመለየት ሪፎርም ለማድረግ ከያዝናቸው ተግባራት መካከል አንዱ የፓርቲ የተቋም ግንባታ ነው ያሉት አቶ ሞገስ፣ ይህንንም በተሟሏ መልኩ ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ስራዎች እየተከናወኑ ነው ሲሉ ጠቅሰዋል።

በከተማዋ ምልከታ ባደረጉባቸው የፓርቲው ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ችግኝ በመትከል አረንጓዴ አሻራቸውን አኑረዋል።
ከነገ ጀምሮ የ2018 በጀት ዓመት የብልጽግና ፓርቲ እቅድ አፈጻጸም እና የ2019 በጀት ዓመት እቅድ ውይይት በአዲስ አበባ ከተማ ይካሄዳል።
በዳንኤል መላኩ