AMN- ሐምሌ 14/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ በዘንድሮው አረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር እስከ አሁን የዕቅዱን 75 በመቶ ማሳካት ተችሏል፡፡
ኢትዮጵያ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋምና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ስታካሂድ የቆየችው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር ሰኔ 7 ቀን 2018 ዓ.ም በይፋ ተጀምሯል፡፡
ተስፋን እንትከል በሚል መሪ ሀሳብ በተጀመረው የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር፣ በአዲስ አበባ ከተማ ለመትከል ከተታቀደው 6 ሚሊየን ችግኞች ውስጥ እስከ አሁን 4 ሚሊየን 469 ሺህ 710 ችግኞች ተተክለዋል።
በዚህም የዘንድሮውን ዕቅድ 75 በመቶ አፈፃፀም ማሳካት መቻሉን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ሰሞኑን መግለፃቸው የሚታወስ ነው።

የዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርኃ-ግብር ዘመቻ ከተለመደው በተለየ ሁኔታ ከዜጎች የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት ጋር በጥብቅ የተቆራኘ ሲሆን፣ ከተተከሉት ችግኞች ውስጥም ከፍተኛውን ድርሻ የሚይዙት እንደ አቮካዶ፣ ማንጎ፣ ፓፓያ፣ አፕል እና ዘይቱን ያሉ የፍራፍሬ ተክሎች እንዲሁም የእንስሳት መኖና የአፈርና ውኃ ጥበቃን የሚያጠናክሩ ናቸው።
መርሐ-ግብሩ የከተማዋን ልምላሜና ውበት ከመጨመሩ ባለፈ፣ የነዋሪዎችን ገቢ ከማሳደግ እና ለወጣቶች የሥራ ዕድል ከመፍጠር ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ውጤት እየታየበት ይገኛል።

ችግኝ መትከል ብቻውን የሚፈለገውን ግብ ስለማያሳካ፣ የተተከሉትን የመንከባከብ ሥራ ጎን ለጎን ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ ነው።
በዚህም መሠረት የችግኞች የጽድቀት መጠን ከ90 በመቶ በላይ ለማድረስ የታቀደ ሲሆን፣ የችግኞችን እድገትና ሁኔታ በዘመናዊ ዲጂታል ቴክኖሎጂ ለመከታተል የሚያስችል አሰራር ተዘርግቶ ዘላቂ የክትትልና የእንክብካቤ ሥራዎች በመከናወን ላይ ናቸው።

በሀገር አቀፍ ደረጃ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሐ-ግብር 8 ቢሊየን ችግኞችን ለመትከል አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቆ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
ኢትዮጵያ ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ባካሄደቻቸው ተከታታይ ዘመቻዎች ከ48 ቢሊየን በላይ ችግኞችን መትከል የቻለች ሲሆን፣ የዘንድሮው መርሐ-ግብር በስኬት ሲጠናቀቅ የተቀመጠውን ግብ በላቀ ሁኔታ የሚያሳካ ይሆናል።
በበረከት ጌታቸው