አዲስ አበባን ውብ፣ ፅዱ እና ለኑሮ የተመቸች ለማድረግ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ ነው – ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ

You are currently viewing አዲስ አበባን ውብ፣ ፅዱ እና ለኑሮ የተመቸች ለማድረግ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ ነው – ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ

AMN- ሐምሌ 18/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባን ውብ፣ ፅዱ እና ለኑሮ የተመቸች ለማድረግ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ እና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጃንጥራር አባይ ገለጹ፡፡

አዲስ አበባን ለአካባቢ ጥበቃና ለዜጎች ጤና ተስማሚ፣ ምቹና ተመራጭ የከተማ ማዕከል ለማድረግ ያለመ “ጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ” የተሰኘ የሦስት ወር ከተማ አቀፍ ንቅናቄ በይፋ ተጀምሯል።

በማስጀመሪያ መርኃ ግብሩ የተገኙት የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ፤ በሶስት ወራት የንቅናቄ መርሃ ግብር የከተማ አስተዳደሩ በአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን አማካኝነት ህብረተሰቡን ባሳተፈ መልኩ የአካባቢ ብክለትን በመከላከልና ህግ በማስከበር ረገድ ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫና የተግባር ስራዎችን እንደሚያከናውን ገልጸዋል።

አዲስ አበባ የአፍሪካ መዲና፣ የፌደራል መንግስቱ መቀመጫና በዓለም አቀፍ ደረጃ ሦስተኛዋ የዲፕሎማሲ ማዕከል መሆኗን የገለጹት ምክትል ከንቲባ አቶ ጃንጥራር አባይ፤ የከተማዋን ገጽታ የሚያሻሽሉ ውብ፣ ፅዱ እና ለኑሮ የተመቸች ለማድረግ ሌት ተቀን የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን ገልጸዋል።

ምክትል ከንቲባው አክለውም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት፣ የኮሪደር ልማት፣ የወንዝ ዳርቻዎችና የፓርኮች ግንባታ ለአየር ንብረት ለውጥ ተግዳሮቶችን ለመቋቋም እና ብክለትን ለመቀነስ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አብራርተዋል።

ሆኖም ከከተማዋ ፈጣን እድገት ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ የፕላስቲክ፣ የአደገኛ ቆሻሻ እና የድምፅ ብክለቶች የዜጎችን በንጹህ አካባቢ የመኖር መብት የሚፃረሩ በመሆናቸው ጠንካራ ቁጥጥርና የጋራ ርብርብ እንደሚያስፈልግ አሳስበዋል።

ለቀጣዮቹ ሦስት ወራት የሚተገበረው የ”ጽዱ ኢትዮጵያ ለትውልድ” ንቅናቄ በዋናነት በፕላስቲክ ብክለት መከላከል፣በአደገኛ ቆሻሻ ብክለት ቁጥጥር እና በድምፅ ብክለት መቀነስ ሦስት ዓበይት የብክለት ዓይነቶች ላይ ትኩረት አድርጎ እንደሚሰራ አቶ ጃንጥራር ገልጸዋል።

ይህ ንቅናቄ ስኬታማ ይሆን ዘንድ መላው የከተማዋ ነዋሪዎች፣ በጎ ፈቃደኞች፣ ሲቪክ ማህበራት፣ ምሁራንና የትምህርት ተቋማት እንዲሁም የመገናኛ ብዙኃን የተጣለባቸውን ታሪካዊና የዜግነት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አቶ ጃንጥራር አሳስበዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review