በመቶ ዓመታት ያልታየ ዕድገት በአምስት ዓመታት – የአዲስ አበባ የጤና ዘርፍ እመረታ

You are currently viewing በመቶ ዓመታት ያልታየ ዕድገት በአምስት ዓመታት – የአዲስ አበባ የጤና ዘርፍ እመረታ

AMN- ሐምሌ18/2018 ዓ.ም

አዲስ አበባን ሁለንተናዊ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ በሚደረገው ጥረት በጤናው ዘርፍ የተመዘገበው ስኬት የጤና አገልግሎት ጥራት እና ተደራሽነት ከፍ እንዲል አድርጓል።

የከተማ አስተዳደሩ መዲናዋን የአፍሪካ የጤና ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ በሰነቀው ትልቅ ራዕይ መሠረት ባለፉት አምስት ዓመታት በተከናወኑ የተቀናጁ ተግባራት ግዙፍ ፕሮጀክቶች ለአገልግሎት በቅተዋል።

በጤና ሥርዓት ውስጥ የሆስፒታል አልጋዎች ቁጥር ለአገልግሎቱ ተደራሽነት እና ዝግጁነት ትልቅ አስተዋጽኦ ያበረክታል። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሥር ባሉ ሆስፒታሎች ቀደም ሲል ይገኝ የነበረው አጠቃላይ የሕክምና አልጋዎች ቁጥር 1ሺህ 384 የነበረ ሲሆን ፣ባለፉት አምስት ዓመታት በተሰራው ሰፊ የማስፋፊያና የአዳዲስ ሆስፒታሎች ግንባታ ቁጥሩ ወደ 4ሺህ 195 ከፍ ብሏል።

ይህ ዕድገት መዲናዋ ባለፉት 100 ዓመታት በጤናው ዘርፍ ካስመዘገበችው አጠቃላይ ዕድገት በላይ ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ ብቻ ማሳካት የቻለችበት ታሪካዊ ስኬት ሆኖ ተመዝግቧል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ለአዳዲስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታሎች ግንባታ እና ለነባር ሆስፒታሎች ማስፋፊያ የሰጠው ልዩ ትኩረት ስኬቱ እንዲመዘገብ ዓይነተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል።

በመዲናዋ 500 አልጋዎች ያሉት የኮልፌ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ፣ 500 አልጋዎች ያሉት የላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል፣ 511 አልጋዎች ያሉት የገላን ድገተኛ ህክምና ሆስፒታል እና 400 አልጋዎች ያሉት የአበበች ጎበና እናቶችና ህጻናት ሆስፒታል አዳዲስ ተገንብተው ለአገልግሎት በቅተዋል።

ነባር ሆስፒታሎች ውስጥ በተከናወነ ማስፋፊያ በዘውዲቱ ሆስፒታል 370 አልጋዎች እንዲሁም በራስ ደስታ ሆስፒታል 230 አልጋዎች ያሏቸው አዳዲስ ህንጻዎች ተገንብተው ወደ ሥራ ገብተዋል።

በዳግማዊ ሚኒሊክ ሆስፒታልም ዘመናዊና ዓለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ የዓይን ህክምና፣ የኩላሊት እጥበት ማዕከል እና የፎረንሲክ አገልግሎት መስጫ ህንጻዎች ተገንብተዋል።

መሰረተ ልማቶችን ከመገንባት ጎን ለጎን የሕክምና አገልግሎት ጥራት ለማረጋገጥም ሆስፒታሎች በዘመናዊ የሕክምና መሳሪያዎች እንዲደራጁ ተደርጓል።

የወረቀት አሰራርን በመቅረፍ የአገልግሎት ቅልጥፍናን የሚያፋጥነው የኤሌክትሮኒክ የጤና መረጃ አያያዝ ስርዓት የተገበሩ የጤና ተቋማት ቁጥርም ከ57 ወደ 68 አድጓል።

የከተማ አስተዳደሩ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት እንደሚያመለክተው ፣ በዓመት ከ1.2 እስከ 1.3 ቢሊዮን ብር በጀት በመደጎም 2.7 ሚሊዮን ነዋሪዎችን የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን ተጠቃሚ ማድረግ ተችሏል።

በአዲስ አበባ ከተማ በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡት እነዚህ ስኬቶች የከተማዋን የጤና አገልግሎት ተደራሽነት እና ጥራት አሳድገዋል። የመዲናዋ ነዋሪዎችም በፍትሃዊነት የህክምና አገልግሎት የሚያገኙበት ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል።

በታደሠ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review