ንቁ የዜግነት ተሳትፎንና ሀገራዊ አንድነትን እያጎለበተ የሚገኘው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት

AMN – ሐምሌ 20/2018 ዓ.ም

የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በየዓመቱ የሚካሄድ ሀገር አቀፍ ዘመቻ ሲሆን፤ በርካታ ዜጎችም በተለያዩ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች ላይ በመሳተፍ ወገናቸውን እና ሀገራቸውን በማገልገል ላይ ይገኛሉ።

መርሐ ግብሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) መሪነት በቤቶች ዕድሳት የተጀመረ ሲሆን፤ ዋነኛ ዓላማውም የበጎ ፈቃደኝነት ባህልን ማጠናከር እና ማኅበራዊ አንድነትን ማጎልበት ነው።

መርሐ ግብሩ ዜጎች ዕውቀታቸውን፣ ጊዜያቸውን ብሎም ጉልበታቸውን የማኅበረሰባቸውን ችግር ለመፍታት እንዲያውሉ ለማበረታታት ነው። አገልግሎቱ በተቀናጀ የሕዝብ ተሳትፎ የመደመር መንግሥትን የልማት ጥረቶች ከማገዙም ባሻገር፤ የኢትዮጵያውያንን የመደጋገፍ፣ የመተባበርና የአንድነት እሴቶች በማጎልበት ላይ ይገኛል።

የዘንድሮው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ጎሮ ወረዳ በይፋ የተጀመረ ሲሆን፤ በመንግሥት የገጠር ኮሪደር ልማት ሥር 20 አዳዲስ የመኖሪያ ቤቶች ግንባታን አካቷል።

ዘንድሮ እየተካሄደ በሚገኘው በዚህ መርሐ ግብር በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች (በተለይም ወጣቶች) ለአቅመ ደካማ እና ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው የኅብረተሰብ ክፍሎች ቤት የማደስና የመገንባት፣ ችግኝ የመትከል፣ አካባቢን የመንከባከብ፣ በሕክምና አገልግሎት እገዛ የማድረግ እና መሰል የበጎ ፈቃድ ሥራዎችን በማከናወን ላይ ይገኛሉ።

በመዲናችን አዲስ አበባም ነዋሪዎች፣ በተለይም ወጣቶች የተሳተፉበት የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት በተቀናጀ መንገድ በመካሄድ ላይ ይገኛል።

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review