AMN – ሐምሌ 21/2018 ዓ.ም
በአዲስ አበባ ከተማ ባለፉት 5ዓመታት ንግድ ሥርዓቱን ለማዘመን እና ገበያውን ለማረጋጋት የተከናወኑ ሥራዎች ተጨባጭ ውጤት ማምጣታቸውን የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ንግድ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ሀቢባ ሲራጅ ገለጹ።
ቢሮው የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማን እና የ2019 ዕቅዶችን አስመልከቶ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል።
በ2018 በጀት ዓመት የንግድ ሥርዓቱን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ በርካታ ተግባራት ስለመከናወናቸው የገለፁት የቢሮ ኃላፊ ፤ በዘመናዊ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት ዘርፍ 16 አገልግሎቶችን በኦንላይን ሥርዓት በማቅረብ በአጠቃላይ 706 ሺህ 855 አገልግሎቶች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ከእነዚህም ውስጥ 105 ሺህ 726 አዲስ የንግድ ፈቃዶች፣ 339 ሺህ 784 የፈቃድ እድሳቶች እና 261 ሺህ 345 ሌሎች አገልግሎቶች እንደሚገኙበት አስረድተዋል።
በንግድ ቁጥጥርና ሕጋዊነት ረገድም 223 ሺህ 760 የንግድ ድርጅቶች የበር ለበር ክትትልና ቁጥጥር የተደረገባቸው ሲሆን፤ በሕገ-ወጥ ንግድ ላይ በተሰማሩ 24 ሺህ 568 የንግድ ድርጅቶች ላይ እርምጃ ተወስዶ፣ 20 ሺህ 617 ነጋዴዎች ወደ ሕጋዊ የንግድ ሥርዓት እንዲመለሱ መደረጉን ገልጸዋል።
በተጨማሪም አገልግሎቶችን በቴክኖሎጂ በመስጠትና የግንዛቤ ሥራዎችን በማጠናከር የሌብነትና የብልሹ አሠራር ችግሮችን በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ መቻሉን እና በዚህ ዘርፍ ጥፋት በፈጸሙ 62 አካላት ላይ ተገቢው እርምጃ መወሰዱን አብራርተዋል።
የምርት አቅርቦትንና የገበያ ማረጋጋትን በተመለከተ በ2013 ዓ.ም. በ5 የገበያ መዳረሻዎች የተጀመረው የቅዳሜና እሁድ ገበያ በ2018 በጀት ዓመት መጨረሻ 264 መዳረሻዎች ላይ መድረሱን አመልክተዋል።

አክለውም 6 የግብርና ምርቶች መሸጫ ማዕከላት ተገንብተው ወደ ሥራ መግባታቸውን የጠቀሱት ወ/ሮ ሀቢባ፤ እነዚህ የገበያ አማራጮች የግብይት ሰንሰለቱን በማሳጠር የኑሮ ውድነት ጫናን ለማቃለል ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ተናግረዋል።
እነዚህ አመርቂ ውጤቶች ቢመዘገቡም የከተማዋ የንግድ ሥርዓት ከሚጠይቀው ደረጃ አንጻር ገና ብዙ የሚቀሩ ሥራዎች እንዳሉ ያመላከቱት ቢሮ ኃላፊዋ፤ የሕገ-ወጥ ንግድን በተሟላ ሁኔታ መከላከል፣ የአቅርቦት ሰንሰለትን ይበልጥ ማሳጠር፣ የገበያ መረጋጋትን ማረጋገጥ፣ የአገልግሎት ጥራትን ማሻሻል፣ የሌብነትና የብልሹ አሠራር ችግሮችን በቀጣይነት መከላከል እና የተቋማዊ አቅምን ማጠናከል በ2019 በጀት ዓመት በትኩረት ሊሰራባቸው የሚገቡ ጉዳዮች መሆናቸውን አስምረውበታል።
በሔለን ጀምበሬ