የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶ ፤ የተለያዩ ዕሳቤዎችና አካሄዶች ከብሔራዊ ጥቅም ጋር ተሳስረዉ የሚጓዙበት ዓመት

You are currently viewing የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶ ፤ የተለያዩ ዕሳቤዎችና አካሄዶች ከብሔራዊ ጥቅም ጋር ተሳስረዉ የሚጓዙበት ዓመት

AMN – መስከረም 4/2019

በቤተሰብ፤ በማህበረሰብ፤ በሃገራዊ እና በሌሎች ጉዳዮች ላይ ልዩነቶችና አለመግባባቶች ሊከሰቱ ይችላሉ፡፡

እነዚህ ልዩነቶችና አለመግባባቶች መከሰታቸዉ ተፈጥሯዊ፤ ያለ እና የነበረ ሲሆን ችግሮቹ የሚፈቱበት የሽምግልናና የምክክር ስርዓትና አካሄድም አላቸዉ፡፡

ኢትዮጵያዊያን ወንድማማችነታቸዉንና አብሮነታቸዉን ጠብቀዉና አስጠብቀዉ ለረጅም ዘመናት አብረዉ የኖሩት ልዩነቶችና አለመግባባቶች ስላልተፈጠሩ ሳይሆን አለመግባባቶቹን በሰለጠነ ባህላዊና ሃይማኖታዊ እሴቶች እየፈቱና እርቅ እየፈጠሩ በመሄዳቸዉ ነዉ፡፡

ከዘመናዊዉ የፖለቲካ ስርዓት ጋር በተያያዘም በርካታ የአለም ሃገራት ዉስጣዊ ልዩነቶቻቸዉን በሰለጠነ መንገድ በመፍታታቸዉ ጠንካራ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ለመገንባት በቅተዋል፡፡

በሃገራችን ኢትዮጵያም በተለያዩ ዘመናት የተፈጠሩ የፖለቲካ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በልሂቃን ጉባዔ ለመፍታት የተሞከረ ቢሆንም ንግግሮቹ ስልጣንን ከመከፋፈል ዉጪ የሃገሪቱን ችግሮች በዘላቂነት ለመቅረፍ አልቻሉም፡፡

ይሁን እንጂ የለዉጡ መንግስት ሃገራዊ ችግሮችን በልሂቃን ድርድር ብቻ ከመፍታት ይልቅ ህዝቡ ራሱ በነገዉ እጣ ፈንታ ላይ መክሮና ዘክሮ የመፍትሔ እርምጃ ያስቀምጥ ብሎ በወሰነዉ ዉሳኔ መሰረት ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ ሃገራዊ የምክክር ጉባዔን አስተናግዳለች፡፡

ጉባኤዉ ህዝቡ ራሱ የምክክሩ ዋና ባለቤትና ተዋናይ የሆነበት ከመሆኑም ባሻገር የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን ያሳተፈ እና በአንድ ቦታ ያገናኘ ልዩ እና ታሪካዊ ጉባዔ ነበር፡፡

የሃገራዊ የምክክር ጉባዔዉ ተሳታሪዎች በተለያዩ አጀንዳዎች ላይ የተግባቡ ሲሆን ስምምነት የተደረሰባቸዉ ጉዳዮች አንድ በአንድ ወደ ተግባር የሚወሰዱ ናቸዉ፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ በምክክር ብቻ የተቋጨ ሳይሆን በአዲስ ዓመት ዋዜማ በመቶ የሚቆጠሩ ታራሚዎች በምሕረት መፈታታቸዉ መንግሥት ለምክክሩ ሐሳቦች ትግበራ ያለውን ቁርጠኝነት ያሳየበት ነዉ፡፡

በዚህ የይቅርታ ሂደት የተፈቱ ወገኖች በሀገራዊ ምክክር ምክረ ሐሳቦች ላይ አዎንታዊ ሚና ይጫወታሉ ተብሎ የሚታመን ሲሆን ካለፈው መንገድ በመማር የወደፊቱን መንገድ የሰላምና የዴሞክራሲ መንገድ ያደርጉታል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበታል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የ2019 የዘመን መለወጫ በዓልን አስመልክተዉ ባስተላለፉት መልእክት ቀጣዩ ዓመት የጉባ ብሥራቶችን የበለጠ ተግባራዊ የምናደርግበት፤ የፖለቲካ ምኅዳሩ ሰፍቶ የተለያዩ ዕሳቤዎችንና አካሄዶችን በብሔራዊ ጥቅም አስተሣሥረን የምንጓዝበት ዓመት ይሆናል ማለታቸዉ የሃገራዊ ምክክሩን ተስፋን ግብ የሚያመላክት ነዉ፡፡

ቀጣዩ አመት ሁለንተናዊ ሉዓላዊነታችን ይበልጥ የሚከበርበት፣ ኅብረ ብሔራዊ አንድነታችን ይበልጥ የሚጸናበት፣ በሁሉም ዘርፎች የጀመርነው ምርታማነት በዓይነትና በጥራት የሚጨምርበት፣ ሀገራችንም የቀጣናውና የአፍሪካ መሪነቷን ሥር መሠረት የምታስይዝበት፤ የኢትዮጵያ ብልጽግና ትውልድ ተሻጋሪ እንዲሆን ተደርጎ የሚገነባበት ዓመት ይሆናል ሲሉም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

በወንድማገኝ አሰፋ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review