AMN- ሐምሌ 22/2018 ዓ.ም
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በ2018 በጀት ዓመት 9 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱን የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ መስፍን ጣሰው አስታወቁ፡፡
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የ2018 በጀት ዓመት የስራ አፈጻጸምን አስመልክቶ አቶ መስፍን ጣሰው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸውም፤ አየር መንገዱ በ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ 20 ነጥብ 7 ሚሊየን ደንበኞችን ማጓጓዝ መቻሉን ጠቁመው በጭነት በኩልም 897 ሺህ ቶን ጭነት ሟጓጓዝ መቻሉን አስታውቀዋል፡፡
አየር መንገዱ ከበረራ መዳረሻዎች አኳያ 4 አዳዲስ ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን በመጨመር ዓለም አቀፍ መዳረሻዎችን ወደ 150 ማድረስ መቻሉን ጠቅሰዋል።

ከሀገር ውስጥ መዳረሻዎች አኳያ፤ በዓመቱ ሶስት መዳረሻዎችን በመጨመር በአጠቃላይ የሀገር ውስጥ መዳረሻዎችን ወደ 25 ማድረስ ስለመቻሉም ገልጸዋል።
ዋና ስራ አስፈጻሚው ፤ ዘጠኝ አዳዲስ አውሮፕላኖችን በግዥና በኪራይ አየር መንገዱ በዓመቱ እንዳስገባ በመግለጽ ስምንት የፓይለት ማሰልጠኛ አውሮፕላኖች መገዛታቸውንም ተናግረዋል።
የቢሾፍቱ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተርሚናልን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በርካታ የመሰረተ ልማት ግንባታ ማስፋፊያ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውንም ጠቅሰዋል፡፡
በንጉሱ በቃሉ