AMN- ነሐሴ 2/2018 ዓ.ም
የህወሓት ቡድን ኢትዮጵያን መበተን ለሚፈልጉ የውጭ ጠላቶች መሣሪያ በመሆን እያገለገለ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገልጸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከኦሮሚያ ብሮድካስቲንግ ኔትወርክ ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ የህወሓት ቡድን የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነትን መጣሱን ተናግረዋል።
የህወሓት ቡድን አሁንም ከግማሽ ክፍለ ዘመን በፊት በነበረው አሮጌ የፖለቲካ አስተሳሰብ እና አመራር ውስጥ ተቀርቅሮ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ቡድኑ ለ27 ዓመታት ሀገርን አስተዳድሮ ከወረደ በኋላም ራሱን እንደ ነጻ አውጪ ግንባር በመቁጠር የትግራይን ሕዝብ ጥቅም ሳይሆን የራሱን ጠባብ የቡድን ፍላጎት ለማስፈጸም እየተንቀሳቀሰ መሆኑን አብራርተዋል።
በሌሎች የኢትይጵያ ክፍሎች የሚገኙ ታጣቂዎችን መጠቀሚያ በማድረግ ሀገርን የማፍረስ ዓላማ ይዞ እየሠራ እንደሚገኝ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ቡድኑ በ1980ዎቹ መጨረሻ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦችን አግልሎ ሥልጣን እንደያዘበት ዓይነት አካሄድ በአሁኑ ወቅት በፍጹም ሊሠራ እንደማይችልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስገንዝበዋል።
ሁሉም የኢትዮጵያ ሕዝቦች አሁን ያሉበት የፖለቲካ ንቃት እና ተሳትፎ ከትናንቱ በእጅጉ የተለየ መሆኑንም ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት የትግራይ ክልል ሙሉ በሙሉ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ እንደሚገኝ እና ፌደራል መንግሥትም ይሁን ሌላ አካል አንድም ሜትር መሬትም ሆነ ሀብት እንዳልወሰደበት ገልጸዋል።
ይህም የቡድኑ ወቅታዊ እንቅስቃሴ ምንም ዓይነት እውነተኛ የሕዝብ ጥያቄን መሠረት ያደረገ አለመሆኑን እንደሚያሳይ አጽንኦት ሰጥተዋል።
ቡድኑ በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያን የማዳከም እና የመበተን የረጅም ጊዜ ስትራቴጂያዊ ፍላጎት ላላቸው ታሪካዊ የውጭ ጠላቶች መሣሪያ በመሆን እያገለገለ ይገኛል ብለዋል።