የወዳጅነት ፓርክ ባለፉት አራት ዓመታት ወደ 1 ቢሊየን ብር ገደማ ገቢ ማስገኘቱ ተገለጸ

You are currently viewing የወዳጅነት ፓርክ ባለፉት አራት ዓመታት ወደ 1 ቢሊየን ብር ገደማ ገቢ ማስገኘቱ ተገለጸ

AMN- ነሐሴ 5/2018 ዓ.ም

በአዲስ አበባ መሐል የሚገኘው የወዳጅነት ፓርክ ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ወደ አንድ ቢሊዮን ብር ገደማ ገቢ አስገኝቷል ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ገለጹ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፣ የወዳጅነት ፓርክ ባለፉት ስምንት ዓመታት በመደመር መንግሥት ከተገነቡት የመጀመሪያዎቹ ዘርፈ-ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የሕዝብ መገልገያ ቦታዎች አንዱ ነው ብለዋል።

በዚህም ፓርኩ ባለፉት አራት ዓመታት ብቻ ወደ አንድ ቢሊየን ብር ገደማ ገቢ ያስገኘ ሲሆን፣ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ የሥራ ዕድሎችንና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን መፍጠሩን አንስተዋል።

ከሁሉም በላይ ደግሞ ከተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች የተውጣጡ ዜጎችና ጎብኝዎች የሚገናኙበት ሥፍራ መሆን መቻሉንም አመላክተዋል።

ከቤተሰቦችና ሕፃናት፣ ከስፖርት ቡድኖችና ከሠርግ ተካፋዮች ጀምሮ እስከ ዲጂታል ይዘት ፈጣሪዎች፣ እንዲሁም የሀገር ውስጥና የውጭ ሀገር ጎብኚዎች በቦታው ይገኙበታል።

የወዳጅነት ፓርክ ከኢኮኖሚያዊ እሴቱ ባሻገር ለጤና፣ ለአካል ብቃት፣ ለመዝናኛና ለሕብረተሰብ ትስስር ትልቅ አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝም ጠቁመዋል።

ይህም በጥሩ ሁኔታ የታቀዱ የሕዝብ መገልገያ ሥፍራዎች ለአዲስ አበባ ከተማ አጠቃላይ የከተማነት ዕድገት አስተዋጽኦ እያበረከቱ ሰዎችን እንዴት ማገናኘት እንደሚችሉ ማረጋገጫ ነው ብለዋል።

ይህ ፓርክ በከተማዋ እንዲሁም በሌሎች ከተሞች ውስጥ እየተገነቡ ላሉ ተመሳሳይ የሕዝብ መገልገያ ሥፍራዎች ቀዳሚ ማሳያ እንደሆነም ገልጸዋል።

እነዚህ አዳዲስ ቦታዎች እሴት የሚፈጥሩ፣ ዕድሎችን የሚያመቻቹ እና ከሁሉም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያውያንን ባለቤትነትን የሚያረጋግጡ ማዕከላት መሆናቸውን አመላክተዋል።

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review