አዲሲቱ የተስፋ አድማስ – የማይገታው የኢትዮጵያ የልማት ጉዞ

AMN – መስከረም 17/2019 ዓ.ም

ኢትዮጵያ አዲስ የታሪክ እጥፋት ውስጥ ትገኛለች። በኢኮኖሚ፣ በማህበራዊና በፖለቲካዊ መስኮች እያስመዘገበችው ያለው ለውጥና ከፍተኛ እድገት በቀጣናውና በአህጉር ደረጃ ጉልህ ተፅዕኖ እየፈጠረ ይገኛል።

የተጠናቀቁና በመገንባት ላይ ያሉ ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶች፣ በጠንካራ ሁኔታ እየተገነቡ ያሉ ተቋማትና ሁሉን አቀፍ እመርታዎች ኢትዮጵያ በአዲስ የልማት ግስጋሴ ውስጥ መሆኗን ያመላክታሉ።

ኢትዮጵያ አዲሷ የተስፋ አድማስ መሆኗን ከሚያረጋግጡ ስኬቶች አንዱ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ነው፡፡ የሀገሪቱን የኃይል ፍላጎት ከመሸፈን አልፎ ለጎረቤት ሀገራት ኃይል ለማቅረብ ያስቻለ፣ የኢትዮጵያውያን የጋራ ጥረትና የሉአላዊነት ምልክት ግዙፍ ፕሮጀክት ነው። ግድቡ ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላትን ተጽእኖም ከፍ ያደረገ አቅም ሆኗል፡፡

በስንዴ ልማት የተመዘገበው ተአምራዊ ስኬት ኢትዮጵያን ከጠባቂነት ወደ ላኪነት የተሸጋገረችበት ታላቅ የልማት አብዮት ሲሆን የምግብ ዋስትናዋን በማረጋገጥ ለኢኮሚያዊ ሉአላዊነት መሠረት ጥሏል፡፡

የገበታ ለሀገር እና ገበታ ለትውልድ ፕሮጀክቶች እንደ ጎርጎራ፣ ወንጪ፣ ኮይሻ እንዲሁም ሃላላ ኬላ እና ሌሎች አስደናቂ የቱሪዝም መዳረሻዎች መጠናቀቅ ያላት የተፈጥሮ ሀብት ወደ ከፍተኛ የኢኮኖሚ አቅም መቀየር እንደምትችል ያረጋገጡ ናቸው።

አንድ ሀገር ዘላቂ እድገት ሊኖረው የሚችለው ጠንካራ ተቋማት ሲኖሩ ብቻ መሆኑን የተረዳው የኢትዮጵያ መንግሥት የተቋማት ግንባታ የሪፎርም ሥራዎችን በልዩ ትኩረት ሲያከናውን ቆይቷል። ኢትዮጵያ ባለፉት ዓመታት የፋይናንስ፣ የህግ፣ የደህንነት እና የአገልግሎት ሰጪ ተቋማቷን ማሻሻልና ማዘመን ላይ ትኩረት በማድረግ ውጤት አስመዝግባለች።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) የተጠነሰሰው የዲጂታል ኢትዮጵያ ኢንሼቲቭ የመንግስት አገልግሎቶችን በዲጂታል መንገድ ተደራሽ በማድረግ የአገልግሎት ቀልጣፋነትን በከፍተኛ ደረጃ በማሻሻል ብልሹ አስራሮችን መቀረፍ ተችሏል።

ኢትዮጵያ የጀመረችው ይህ ሁለንተናዊ እመርታ በጠንካራ ህዝባዊ ትብብርና በአድማስ ተሸጋሪ ሀገራዊ ራዕይ ነው እየተገነባ የሚገኘው። ያሉ መልካም አጋጣሚዎችን በመጠቀም፣ ፈተናዎችን በመቋቋም የብልፅግና ጎዳናዋን እያፋጠነች ትገኛለች።

በውስጥም ሆነ በውጭ ይህን የኢትዮጵያን ግስጋሴ ለማደናቀፍ የሚፍጨረጨሩ ቢኖሩም፣ የኢትዮጵያ ህዝብና መንግስት የገነቡት የፅናት ባህልና እየተመዘገበ ያለው ተጨባጭ ውጤት የተቀጣጠለውን የኢትዮጵያን የብልፅግና ማዕበል የሚያስቆም አይሆንም፡፡

ባለፉት ዓመታት ተግዳሮቶችን ወደ ዕድል በመቀየር የተሻገረችበት ብልሃት ኢትዮጵያ ፈተናዎችን መቋቋም የሚችል አቅም ያላት መሆኗን አረጋጋጭ ናቸው፡፡

ውሾቹ ቢጮሁም ግመሎቹ ጉዟቸው እንደማይገታው ሁሉ፣ እዚህም እዚያም አይቀሬውን የኢትዮጵያ ብልጽግና ለማደናቀፍ መውተርተሮችን ወደ ኋላ ትታ ኢትዮጵያ የያዘችውን ልማትና የእድገት አቅጣጫ አስጠብቃ ወደፊት መገስገሷን ትቀጥላለች።

በታደሰ ሽፈራው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review