AMN- ነሐሴ 5/2018 ዓ.ም
የሀገሪቱን ዲጂታል ሉዓላዊነት በጠንካራ መሠረት ላይ ለመገንባት የሚያስችለው 5ኛው ዙር የሳይበር ታለንት ሰመር ካምፕ በአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ በይፋ ተጀምሯል፡፡
በመርሐ-ግብሩ ላይ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር (ኢመደአ) ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ትዕግስት ሃሚድ፤ የዲጂታል ደህንነት የሀገር ህልውና መሠረት መሆኑን አፅንዖት ሰጥተዋል።
የሳይበር ደህንነት ከፍተኛ ሥነ-ምግባርን የሚጠይቅ በመሆኑ ዕውቀታችሁን ለሀገር ግንባታና ለበጎ ዓላማ ብቻ አውሉት ሲሉም ለተመረጡት ሰልጣኞች መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
እርስ በርስ በመቀራረብና የጋራ ፕሮጀክቶችን በመቅረጽም የቤተሰባዊነት መንፈስን እንዲፈጥሩ አደራ ብለዋል።
የአዲስ አበባ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት አስራት አጸደወይን (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ በነገ ሀገር መሪዎች ላይ የሚደረገው ይህ ኢንቨስትመንት ለኢትዮጵያ ዲጂታል ሉዓላዊነት ጠንካራ መሰረት የሚጥልና ወጣቶቹን የዲጂታሉ ዘመን ቀዳሚ መሪዎች እንደሚያደርጋቸው ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

የኢመደአ የሳይበር ልህቀት ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ቢሻው በየነ የዘንድሮውን ካምፕ አጠቃላይ ዝግጅት ሪፖርት አቅርበዋል።
ቀደም ሲል በ2 ዩኒቨርሲቲዎች ብቻ ይሰጥ የነበረው ይህ መርሐ-ግብር፣ ዘንድሮ አድማሱን በማስፋት በ7 ማዕከላት እየተሰጠ ይገኛል፡፡
ስልጠናው በአዲስ አበባ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ፣ ባሕር ዳር፣ ሐረማያ፣ ጅማ፣ ደብረ ብርሃን እና ወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲዎች እንዲሁም በኢመደአ የታለንት ማዕከል በመሰጠት ላይ ነው።
ለዚህ መርሐ-ግብር ከ14 ሺህ በላይ ወጣቶች መመዝገባቸው፣ ትውልዱ ለዘርፉ ያለውን ከፍተኛ ፍላጎት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ (ዶ/ር) ባስተላለፉት የ “5 ሚሊየን ኢትዮጵያውያን ኮደርስ” ሀገራዊ ጥሪ ላይ የታየውን መነቃቃት የሚያጠናክር መሆኑ የዘንድሮውን ልዩ እንደሚያደርገው ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አስተዳደር የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡