AMN – ነሐሴ 7/2018 ዓ.ም
የዛሬ ህጻናት የነገ ሀገር ተረካቢዎች ናቸው፡፡ የነገ ሀገር ተረካቢዎች ደግሞ በአካልም በአዕምሮም ብቁ እንዲሆኑ የልጅነት እድገት ላይ አተኩሮ መስራት ከሁሉ በላይ ቀዳሚ ግብ ማድረግ ይገባል፡፡
ለዚህም ነው አዲስ አበባ የነገ ሀገር ተረካቢ ህጻናትን ከፅንሰት ጀምሮ እስከ 6 ዓመታቸው ትክክለኛ እድገት እንዲኖራቸው የቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ቀርጻ ተግባራዊ እያደረገች የምትገኘው፡፡
በቀዳማይ ልጅነት ልማት ፕሮግራም ባለፉት አምስት ዓመታት በከተማችን 1.3 ሚሊዮን ገደማ ህጻናትን ተጠቃሚ ለማድረግ ግብ ተጥሎ የተሰራ ሲሆን ፣ አምስት አንኳር ጉዳዮችን ያካተተ የቀዳማይ ልጅነት ልማት ተግባራዊ ተደርጓል፡፡
በዚህ ፕሮግራም ለወላጆች እና አሳዳጊዎች የምክር አገልግሎት የሚሰጡ ከ5 ሺህ በላይ ሰራተኞችን በማሰልጠንና በማሰማራት የቤት ለቤት የምክር አገልግሎት እንዲሰጡ ተደርጓል፡፡
ለትውልድ ግንባታ ጠንካራ መሰረት የሚጥሉ 1ሺህ 155 የህጻናት ማቆያዎች ተገንብተውና ተደራጀተው አገልግሎት በመስጠት ላይ ናቸው፡፡

ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸውና በአስር ሺዎች ለሚቆጠሩ እናቶች እና ህጻናት ተከታታይ የአልሚ ምግብ ድጋፍና ክትትል እየተደረገ ነው። በክትትሉ የእድገት ውስንነት የታየባቸው ሁሉም ህጻናት ተገቢውን የህክምና ክትትል እንዲያገኙ ተደርጓል፡፡
ህፃናቱ ለመደበኛ ትምህርት ዝግጁነት በጨዋታ መልክ እንዲማሩ ለማድረግ በተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆን ችለዋል፡፡
በቀዳማይ ልጅነት ልማት ዛሬ ለወላጆቻቸው እፎይታን ፣ ለልጆች ደግሞ የወደፊት ብሩህ ተስፋን ያስገኙ ውጤቶች መመዝገባቸው በጥናት ጭምር መረጋገጡን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ ያመላክታል።