AMN – ነሐሴ 8 /2018
በአዲስ አበባ የሚከናወኑ አስደናቂ የልማት ሥራዎች መንግሥት የዜጎችን የኑሮ ዘይቤ ለማሻሻል የሚያደርገውን ቁርጠኛ አቋም የሚያሳይ መሆኑን ጎብኚዎች እና ነዋሪዎች ተናግረዋል።
በመዲናዋ ከተሰሩት ፕሮጀክቶች መካከል አንዱ የቀበና ወንዝ የቀድሞ ገጽታ በመቀየሩ ምክንያት ልዩ ልዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በቀን እና በምሽትም የሚዝናኑበት፣ የሚያሰላስሉበት እና ማህበራዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን የሚከውኑበት ማራኪ ስፍራ ሆኗል።
የቱሪስት አስጎብኚዋ ምሕረት አሰፋ እንደገለፁት፣ በአዲስ አበባ በጥቂት ዓመታት ውስጥ የተከናወኑት የልማት ስራዎች እጅግ አስደናቂ ናቸው።
በሌሎች አገራት በጉብኝት ወቅት የተመለከቷቸውን የከተማ ልማት ስራዎች በኢትዮጵያም ማየታቸው እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል።
የቀድሞው የቀበና ወንዝ አካባቢ በቆሻሻ የተሞላ እንደነበር የሚያስታውሱት ሌላኛው የአዲስ አበባ ነዋሪ መለሰ ከበደ፣ አሁን ላይ ግን አካባቢው ውብ እና ለኑሮ ተስማሚ መሆን መቻሉን ተናግረዋል።

ይህ የልማት ስራ ዘርፈ ብዙ ጥቅሞች ያሉት በመሆኑ፣ ለቱሪዝም እና ለወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ ምቹ ሁኔታን የፈጠረ መሆኑም አንስተዋል።
በአካባቢው እንደመኖራቸው መጠን ከቤተሰባቸው ጋር በመሆን በቀበና ወንዝ አካባቢ የሚያሳልፉት ጊዜ እጅግ አዝናኝ እና አስደሳች መሆኑንም ገልጸዋል።
እሸቱ አማረ በበኩላቸው፣ ቀደም ባሉት ጊዜያት በአዲስ አበባ እንዲህ ያሉ ዘመናዊ የመዝናኛ ሥፍራዎች እጥረት በመኖሩ ነዋሪዎች ከከተማ ውጭ ወደ ሆኑ አካባቢዎች ለመሄድ ይገደዱ እንደነበር አስታውሰዋል።
በተለይም ህጻናት አእምሯቸውን የሚያድሱበትና ንጹህ አየር የሚያገኙበት በመሆኑ ለዕድገታቸውም ሆነ ለጤናቸው ከፍተኛ ጠቀሜታ እንዳለው አንስተዋል።
ከአራት ዓመት በኋላ ዳግም አዲስ አበባን የጎበኙት ከድሬዳዋ የመጡት ሁስኒያ አብዲ፣ የከተማዋ ገጽታ በኮሪደር ልማት ስራዎች ተቀይሮ መመልከታቸው እንዳስደነቃቸው ተናግረዋል።
በዋና ዋና መንገዶች ላይ የተከናወኑት የኮሪደር ልማት እና የጽዳት አጠባበቅ ከተማዋን እጅግ ውብ እና ሳቢ እንዳደረጓትም ገልጸዋል።
ከባሌ ሮቤ የመጡት ሁሴን አህመድ፣ ከጥቂት ዓመታት በፊት በነበረው እና አሁን ባለው የከተማዋ ዕድገት መካከል ያለውን ልዩነት በግልጽ መመልከታቸውን ገልጸዋል።

በስራ ምክንያት አድካሚ ቀናትን የሚያሳልፉ የተለያዩ ሰራተኞች፣ ከስራ ውጪ አእምሯቸውን ዘና የሚያደርጉበትና የሚያሳርፉበት ቦታ ማግኘታቸው እጅግ አስደሳች መሆኑን ተናግረዋል።
የልማት ፕሮጀክቶቹ ለአዲስ አበባ ውበትን ከማጎናጸፍ ባለፈ የቱሪዝም መዳረሻ በመሆን ለሀገራችን ዕድገት ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ መናገራቸውን ኢዜአ በዘገባው ጠቅሷል።