የአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች ከዛሬ ጀምሮ ይመለሳሉ ፤ ዘንድሮ ምን ይጠበቃል?

AMN- ነሐሴ 9/2018 ዓ.ም

የአውሮፓ ታላላቅ አምስት ሊጎች የ2026/27 የውድድር ዓመታቸውን ዛሬ ይጀምራሉ። ዓለም አቀፍ ተቀባይነታቸው ከፍ ያለው እነዚህ ሊጎች ዘንድሮ ምን ያስመለክቱን ይሆናል?

👉 ከፍተኛ ፉክክር የሚጠበቅበት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ

በአውሮፓ እንደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ዓለም አቀፍ ተቀባይነቱን ያሰፋ ሊግ ማግኘት ይከብዳል። ለዚህ ትልቁ ምክንያት የፉክክር ደረጃው ከፍ ያለ መሆኑ ነው።

ከ22 ዓመት በኋላ የሊጉ አሸናፊ ሆኖ ደጋፊዎችን ያስፈነጠዘው አርሰናል ዘንድሮም ለድል ታጭቷል።

መድፈኞቹ እስካሁን በፈለጉት ልክ ስብስባቸውን ባያጠናክሩም ለተከታታይ ዓመት የሊጉ አሸናፊ የመሆን አቅም እንዳላቸው ተገምቷል።

ፔፕ ጋርዲዮላን በኢንዞ ማሬስካ የተካው ማንችስተር ሲቲ አርሰናልን የመቀናቀን አቅም አለው ተብሎለታል።

ምንም እንኳን በዝውውሩ በስፋት ባይሳተፍም በማይክል ካሪክ የተረጋጋ ጊዜ ላይ የሚገኘው ማንችስተር ዩናይትድንም የገመቱ አልጠፉም።

በቻቢ አሎንሶ የሚሰለጥነው ቼልሲ እና በቀድሞ የቦርንማውዝ አሰልጣኝ አንዶኒ ኢራዮላ የሚመረው ሊቨርፑል በየትኛውም የውድድር ዓመት እንደሚሆነው ለግምት ቀርበዋል።

ቶተንሃም ሆትስፐርስም ካስፈረማቸው የተጫዋቾች ጥራት እና አሰልጣኙ ሮቤርቶ ዲ ዘርቢ ምክንያት የፉክክር ደረጃውን ከፍ ያደርጋል ተብሎ ይጠበቃል።

የውድድር ዓመቱ የፊታችን አርብ አርሰናል ከ ኮቨንትሪ ሲቲ በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራል።

👉 ጆዜ ሞሪንሆን የመለሰው የስፔን ላሊጋ

ጆዜ ሞሪንሆ ከ13 ዓመት በኋላ ወደ ሪያል ማድሪድ ተመልሰዋል። የፖርቹጋላዊው አሰልጣኝ መመለስ ላሊጋው የተለየ የፉክክር ጣዕም ማየቱ የማይቀር ነው።

ማድሪድ የባለፉትን ሁለት የውድድር ዓመታት የባርሰሎናን የበላይነት ለመግታት ያን ዲዮማንዴን የክለቡ ውዱ ፈራሚ አድርጎ አምጥቷል።

ማርክ ኩኩሬያ ፣ ዴንዘል ዱምፍሪስ ፣ ኢብራሂማ ኮናቴ እና በርናርዶ ሲልቫንም ወደ ስብስቡ ቀላቅሏል። ወሳኝ ተጫዋቹ ቪኒሺየስ ጁኑዮርም ውሉን አራዝሟል።

ጆዜ ሞሪንሆ የቡድኑን ሚዛናዊነት ከጠበቁ ስኬታማ ሊያደርጋቸው የሚችል ስብስብ አላቸው።

ባርሰሎና አሁንም ለዋንጫ የሚገመት ክለብ ነው። በሀንሲ ፍሊክ እየተመራ ያለፉትን ሁለት የላሊጋ ዋንጫዎች ያነሳው ባርሳ አጥቂ ክፍሉን ማጠናከር ይጠበቅበታል።

የሮቤርት ሌቫንዶቭስኪ መልቀቅ ፣ የፌራን ቶሬስ ወደ ፓሪሰን ዠርማ ለማምራት መቃረብ እና የማርከስ ራሽፎርድ የውሰት ውሉን ጨርሶ ወደ ማንችስተር ዩናይትድ መመለስ አጥቂ ፍለጋ ወደ ገቢያው እንዲወጡ ያስገድደዋል።

የማንችስተር ሲቲውን አማካይ ሮድሪ ለማምጣት እየጣረ የሚገኘው ክለቡ አንቶኒ ጎርደንን እና ካሪም አዴዬሚን ማስፈረሙ ይታወሳል።

አትሌቲኮ ማድሪድ ለዓመታት እንዳደረገው ሁለቱን ሃያላን ለመፎካከር ተዘጋጅቷል። ላሊጋውን የማሸነፍ አቅም አለው የሚል ግምት ግን አልተሰጠውም።

ዛሬ ምሽት 2:30 ዲፖርቲቮ አላቬስ ከ ሄታፌ የሚያደርጉት ጨዋታ የውድድር ዓመቱን ይከፍታል።

👉 በጉጉት የሚጠበቀው የጣልያን ሴሪ አ

ኢንተር ሚላን ለሁለተኛ ተከታታይ ዓመት የሊጉ አሸናፊ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል። በክሪስቲያን ኪቩ የሚመራው ኢንተር ከሌሎች ክለቦች አንፃር የተሻለ ስብስብ እና መረጋጋት አለው።

ናፖሊ ፣ ሚላን ፣ አታላንታ እና ላዚዮ የውድድር ዓመታቸውን በአዳዲስ አሰልጣኞች ይጀምራሉ።

የቀድሞ የማንችስተር ዩናይትድ አሰልጣኝ ሩበን አሞሪምን የሾመው ሚላን እና በሉቺያኖ ስፓሌቲ የሚመራው ጁቬንቱስ ኢንተርን የመፎካከር አቅም አላቸው ተብሎላቸዋል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ተዓምር አሳይቶ የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ተሳታፊ የሆነው የሴስክ ፋብሪጋሱ ኮሞ ዘንድሮ ምን ያሳያል የሚለው ለማየት ያጓጓል።

ኡዲኒዝ ከ ኮሞ ፤ ኢንተር ሚላን ከ ሞንዛ የዛሬ ሳምንት የሚያደርጓቸው ጨዋታዎች የሴሪ አውን መጀመር ያበስራሉ።

👉 የባየርን ሙኒክን የበላይነት የሚገታ ክለብ የሚፈልገው የጀርመን ቡንደስሊጋ

የጀርመን ቡንደስሊጋ አሁንም በባየርን ሙኒክ የበላይነት የሚቀጥል ይመስላል። የቪንሰንት ኮምፓኒ ቡድን ስብስቡ አሁንም አስፈሪ ነው።

ጀርመን ከደረሰ በኋላ ነገሮች አልጋ በአልጋ የሆኑለት ሀሪ ኬን ከ94 የቡንደስ ሊጋ ጨዋታ 98 ግቦችን በስሙ አስመዝግቧል። የ33 ዓመቱ እንግሊዛዊ አጥቂ ዘንድሮም ለሌላ ታሪክ እራሱን አዘጋጅቷል።

ቦሩሲያ ዶርትመንድ ፣ አር ቢ ላይብዚግ እና ባየር ሊቨርኩሰን በመጠኑ የመፎካከር አቅም ያላቸው ክለቦች ይመስላሉ።

የ2026/27 የውድድር ዓመት የጀርመን ቡንደስ ሊጋ ከሁለት ሳምንት በኋላ ባየርን ሙኒክ ከ ስቱትጋርት በሚያደርጉት ጨዋታ ይጀምራል።

👉 ፓሪሰን ዠርማ የበላይነቱን ለማስጠበቅ የሚጥርበት የፍሬንች ሊግ ኧ

የሊውስ ኤነሪኬው ፓሪሰን ዠርማ ከፍሬንች ሊግ የገዘፈ ሆኗል። ይህንንም ሁለት ተከታታይ ዓመት የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግን በማንሳት አስመስክሯል።

ፓሪሰን ዠርማ ከመጨረሻዎቹ 14 የውድድር ዓመታት 12ቱን ያጠናቀቀው የሊጉ የበላይ ሆኖ ነው። ዘንድሮም ይህን ማስቀጠሉ የማይቀር ይመስላል።

በተጠናቀቀው የውድድር ዓመት ፓሪሰን ዠርማ ለመፎካከር የጣረው ሎንስ አሰልጣኙን እና የተወሰኑ ወሳኝ ተጫዋቾችን አጥቷል።

ሊል ፣ ማርሴይ እና ሞናኮም በአዲስ አሰልጣኝ መቅረባቸው የበለጠ ለፓሪሰን ዠርማ ነገሮችን ቀላል የሚያደርግ ይመስላል።

የፊታችን አርብ ማርሴይ ከ ስትራስቡርግ የሚያደርጉት ጨዋታ የውድድር ዓመቱን ጅማሮ ይፋ ያደርጋል።

በሸዋንግዛው ግርማ

See less

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review