የሕፃናት የቴክኖሎጂ አጠቃቀምና ወላጆች ሊያውቁት የሚገባው ሥነ-ልቦናዊ ተጽዕኖ

AMN- ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም

በአሁኑ ሰዓት ቴክኖሎጂ የዕለት ተዕለት ሕይወታችን ዋና አካል ሆኗል፤ ይሁን እንጂ የቴክኖሎጂ እና የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም በህጻናት አስተዳደግ፣ ሥነ-ልቦና እና ማህበራዊ ህይወት ላይ እያደረሰ ያለው ተጽዕኖ ከጊዜ ወደ ጊዜ አሳሳቢ እየሆነ መጥቷል።

በአለርት ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል የአዕምሮ ህክምና ባለሙያ የሆኑት አቶ ጃማል ሐሰን ከኤ ኤም ኤን ጋር በነበራቸው ቆይታ፣ ይህንን አሳሳቢ ጉዳይ አስመልክቶ ጥልቅ ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የቴክኖሎጂ ከመጠን ያለፈ አጠቃቀም በህፃናት ላይ የሚያስከትላቸው ተፅዕኖዎች

ህፃናት እድሜያቸውን በማይመጥን መልኩ እና ለረጅም ሰዓታት ቴክኖሎጂን በሚጠቀሙበት ጊዜ፣ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ የሚለቀቁ የተጋነኑ የድምፅም ሆነ የምስል መረጃዎችን ሊመለከቱ ይችላሉ።

ይህም የተሳሳተ ግንዛቤ ፈጥሮ የበታችነት ስሜት እንዲያዳብሩ በማድረግ የእውነት እና የምናባዊ ዓለም መምታታትን ይፈጥርባቸዋል ብለዋል።

የማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም እየጨመረ በሄደ ቁጥር ከቤተሰብ፣ ከትምህርት ቤት ጓደኞች እና ከማህበረሰቡ ጋር የሚደረግ ግንኙነት እያነሰ በመሄድ የማህበራዊ መስተጋብር መቀነስን ያመጣል፡፡

ሕፃናት ሙሉ ሕይወታቸው ማህበራዊ ሚዲያ ላይ እንዳለ አድርገው ማሰብ ሲጀምሩ፣ የትምህርት ትኩረታቸው ይሰረቃል፣ የቤት ስራዎችንና የክፍል ውስጥ ስራዎችን በአግባቡ ለመወጣት ይቸገራሉ፣ በመጨረሻም የትምህርት ውጤታቸው ዝቅተኛ ይሆናል በማለት ባለሞያው ያስገነዝባሉ።

በሕይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በውይይት ወይም በማህበራዊ ድጋፍ የመፍታት አቅማቸው እየቀነሰ ስለሚመጣ እና ከዚህም አልፎ ጭንቀት የመሳሰሉ የአእምሮ ጤና ችግሮች እና ችግሮችን የመቋቋም አቅም መዳከም ሊያጋጥሟቸው እንደሚችሉም ይገልፃሉ።

በተጨማሪም የስሜት እድገት መጓተት ማለትም ራሱን የመረዳት አቅም መቀነስ፣ የማህበራዊ እውነታዎችን አለማስተዋል፣ ምክንያታዊ ውሳኔዎችን የመወሰን አቅም መዳከም፣ ከቤተሰብ እና ከሌሎች ሰዎች ጋር ጤናማ እና ውጤታማ ማህበራዊ ግንኙነት መመስረት ላይ ከፍተኛ ችግር እንደሚያሳዩ አመላክተዋል።

የወላጆች እና የአሳዳጊዎች ኃላፊነት

ወላጆች የራሰን አጠቃቀም መገምገም፣ ህጻናትን ከማስተማራችን በፊት እኛ ራሳችን ቴክኖሎጂን እንዴት እየተጠቀምንበት እንደሆነ መፈተሸ ይገባል የሚሉት ባለሙያው፣ ለጥሩ ነው ወይስ ለተሳሳተ ዓላማ? የሚለውን በንቃት መረዳት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል።

ለልጆቻችን የሚሰጠው ቴክኖሎጂ ከእድሜያቸው እና ከትምህርት ደረጃቸው ጋር የሚሄድ መሆኑን በጥንቃቄ መረዳትና መቆጣጠር እንደሚገባም ያስረዳሉ።

በሂደቱ ለይቶ ለማወቅ ወይም ለመቆጣጠር የሚከብድ ከሆነ፣ በማህበራዊ ሚዲያ አጠቃቀም ዙሪያ ምክር የሚሰጡ ባለሙያዎችን ማማከር ጠቃሚ እንደሆነም ያነሳሉ።

የቴክኖሎጂ አጠቃቀማችንን ጤናማ፣ ከሕይወታችን፣ ከባህላችን እና ከትምህርታችን ጋር የሚሄድ በማድረግ ማህበራዊ ሚዲያን ለተፈለገውና ጠቃሚ ለሆነ ዓላማ ብቻ ማዋል የሁላችንም ኃላፊነት ሊሆን ይገባል ሲሉም ይመከራሉ።

በፍሬሕይወት ብርሃኑ

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review