AMN- ነሐሴ 11/2018 ዓ.ም

የአዲስ አበባ የቱሪስት መዳረሻ ልማቶች ከተማዋን ተወዳዳሪ የቱሪዝም ማዕከል እያደረጓት መሆኑን ዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ገለጹ፡፡
መንግስት በሃገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው ብዝሃ ኢኮኖሚን ለማሳደግ ካስቀመጣቸው አምስት የልማት ምሰሶዎች መካከል የቱሪዝም ዘርፉ አንዱ ነው፡፡

ቤልጀማዊው ጎብኚ ዴሪክ ዴሌ አንዱሉት፤ የአዲስ አበባ አስደናቂ ውበት፣ ጽዳት እና የህዝቡ እንግዳ ተቀባይነት ጎብኝዎች ቆይታቸውን እንዲያራዝሙና በሌላ ጊዜ ተመልሰው ለመምጣት እንዲያስቡ ያደርጋል፡፡

በቆይታቸውም እንጦጦ ፓርክንና ብሄራዊ ሙዚየምን መጎብኘታቸውን ገልጸው የሆቴል አገልግሎቶቹ የኢትዮጵያውያንን እንግዳ ተቀባይነት በጉልህ እንደሚያሳዩ ተናግረዋል፡፡

ጣሊያናዊው አሌሳንድሮ ቦዞ በበኩላቸው፤ከ20 አመት በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥተው እንደነበር በማስታወስ አሁን ከተማዋ ፈጣንና ማራኪ ለውጥ እያስመዘገበች መሆኑን ገልጸዋል።

ታሪካዊ ቅርሶችን በውስጡ የያዘውን ብሄራዊ ሙዚየምን እንደጎበኙ በማንሳት፤ የከተማዋን ውበትና ንጽህናም አድንቀዋል፡፡
በመዝናኛ ሥፍራዎችም የእረፍት ጊዜን ማሳለፍ እንደሚቻል ጠቅሰው በአረንጓዴ ስፍራዎችና በወንዞች ማራኪ ፍሰት የማይረሳ ጊዜ ማሳለፍ እንደሚቻል ገልጸዋል።

ሌላኛው ጀርመናዊው ሎካስ ኩፕፈርናጌል፤ በአዲስ አበባና በሌሎች አካባቢዎች በቱሪዝም ዘርፍ የተመዘገቡ ውጤቶች አስገራሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአዲስ አበባ ፈጣን የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት ከተማዋን ለዓለም አቀፍ ጎብኝዎች ምቹና ማራኪ እንዳደረጋት የገለጹት ደግሞ ጀርመናዊው ሄርማን ግሬሆ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ ግንባር ቀደም የቱሪስት መዳረሻ እየሆነች መጥታለችም ብለዋል። በኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የሚደረጉ እንቅስቃሴዎች የቱሪዝም ዘርፉን እያሳደጉ መሆኑን በመግለጽ ይሄም ሃገሪቱን በአፍሪካ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ማዕከል የሚያደርጋት መሆኑን አንስተዋል፡፡
በአዲስ አበባ የተከናወነው ሥራ ትውልድን የሚያኮራ መሆኑንም መመልከታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም በተለያዩ ዘመናትና ወቅቶች ውስጥ ያለፈውን የኢትዮጵያን ታሪክ መመልከት ደስታን የሚፈጥር እና እጅግ አስደናቂ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በወርቅነህ አቢዮ