ኢትዮጵያ – የሰው ዘር መገኛ እና የዓለም የትኩረት ማዕከል

You are currently viewing ኢትዮጵያ – የሰው ዘር መገኛ እና የዓለም የትኩረት ማዕከል

AMN – ነሐሴ 13/2018 ዓ.ም

ኢትዮጵያ የሰው ዘር መገኛ መሆኗን የሚያረጋግጡ ታሪካዊ እውነታዎች በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ እውቅናን አትርፈውላታል።

የዘመናት ታሪክ ተናጋሪ የሆኑት ድንቅነሽ (ሉሲ) እና አርዲ፣ እንዲሁም በኦሞ ኪቢሽ እና በሀዳር ምድር የተገኙት ጥንታዊ ቅሪተ አካላት ሀገሪቱን የሰው ዘር መነሻ ማዕከል አድርገዋታል።

ይህን ታሪካዊ እውነት ተከትሎ ዓለም አቀፍ የዘርፉ ተመራማሪዎች እይታቸውን ወደ ኢትዮጵያ በማዞር የሰው ዘርን የጥንት ታሪክ በጥልቀት በመመርመር ላይ ይገኛሉ።

እንደ ናሽናል ጂኦግራፊ እና ቢቢሲ ያሉ ታዋቂ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎችም የሰው ልጆችን ታሪክ ሲዘግቡ መነሻቸውን ወደዚች ታሪካዊት ምድር በማድረግ መዘገባቸው፤ ሀገሪቱ በዓለም አቀፍ መድረኮች ያላትን አዎንታዊ ገጽታ ከመገንባቱም በላይ የቱሪዝም ዘርፉን በከፍተኛ ደረጃ እያነቃቃው ነው።

የሰው ዘር መገኛ የሆነችውን ይህችን ውብ ሀገር ለመረገጥ እና የቅድመ-ታሪክ ምስጢሮቿን ለመቃኘት የሚጓጉ ተጓዦች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው።

የቅሪተ አካል መገኛ ስፍራዎችም ለሀገር ውስጥና ለውጭ ቱሪዝም ክፍት መሆናቸው የአካባቢውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ከማድረጉ ባለፈ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ወሳኝ ሚና እየተጫወቱ ይገኛሉ።

ሀገሪቱ የዓለም አቀፍ ተጓዦች መዳረሻ ብቻ ሳትሆን ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገረው የጋራ ታሪካችን አምድ ሆና ቀጥላለች።

ይህን ትልቅ ዓለም አቀፍ የቱሪዝም እምቅ አቅም ይበልጥ ለማሳደግ እና የሀገሪቱን ገጽታ ከፍ ለማድረግ፣ ይህንን ድንቅ ታሪክ መንከባከብና በላቀ ደረጃ ለዓለም ለማስተዋወቅ ከዘርፉ ማግኘት ያለባት ጥቅም እንድታገኝ የተቀናጀ ጥረትን ይጠይቃል።

በበረከት ጌታቸው

0 Reviews ( 0 out of 0 )

Write a Review