AMN- ነሐሴ 16/2018 ዓ.ም

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ የማጠቃለያ ሥነ ሥርዓት በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በደማቅ ሁኔታ እየተካሄደ ነው።
በምምክሩ ኢትዮጵያዊያን ለዘመናት ያጋጠሟቸውን ታሪካዊ ስብራቶችና የሐሳብ ልዩነቶች በመገፋፋት ሳይሆን በመደማመጥ መፍታት የሚችሉበት አዲስ የፖለቲካ ባሕል ተፈጥሯል።
በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምክትል ዋና ኮሚሽነር ሂሩት ገብረሥላሴ፣ ከአራቱም የሀገሪቱ ማዕዘናት የተውጣጡ አራት ሺህ የሚሆኑ ተመካካሪዎች በኃላፊነት ስሜት መሳተፋቸውን አስታውሰዋል።
የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የቀድሞ ታጣቂዎች፣ የዳያስፖራ ማኅበረሰብ አባላት፣ የሃይማኖት ተቋማት እና ታዋቂ ሰዎች በአንድነት የተሰባሰቡበት ይህ መድረክ፣ የመላው ኢትዮጵያውያን እውነተኛ የውይይት ማዕከል መሆን መቻሉንም አብራርተዋል።
በምምክሩ ወቅት ጥልቅ የሀሳብ ልዩነቶች ቢንጸባረቁበትም፣ ተሳታፊዎች ከራሳቸው አመለካከት በላይ የሀገሪቱን የጋራ ጥቅም በማስቀደም ውይይቱን ማጠናቀቃቸውን ገለፀዋል።

ሀገሪቱን አሁን ካለችበት ስብራት አውጥተው ወደ አዲስ ምዕራፍ የሚያሻግሩ እጅግ የላቁ የምክር ሀሳቦች መፍለቃቸውንም አብራርተዋል።
ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች የተገኙት የምክር ሀሳቦች በመንግሥት እና በሚመለከታቸው አካላት አማካኝነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረጉ ያላቸውን እምነትም ገልፀዋል።
የምንለያይበት ጉዳይ ቢኖርም የምንጋራት ሀገር አንዲት ናት፤ የምንፈልገውም ለቀጣዩ ትውልድ የተረጋጋች፣ ሰላማዊ እና የበለጸገች ኢትዮጵያን ማስተላለፍ ነው ሲሉም አንስተዋል፡፡
ኮሚሽኑ ይህንን ታሪካዊ ሂደት በስኬት እንዲያጠናቅቅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የፌደራል እና የክልል መንግሥታት፣ የከተማ አስተዳደሮች፣ የጸጥታ አካላት፣ የሚዲያ አጋሮች እና ለመላው ተሳታፊዎች ምክትል ኮሚሽነሯ ምስጋና አቅርበዋል።
የተጀመረው የመደማመጥ ባህል አብቦ ለትውልድ የሚሻገር ዘላቂ እሴት እንዲሆን የሁሉንም ዜጋ ተሳትፎ እንደሚጠይቅም አመላክተዋል።
በበረከት ጌታቸው