AMN- ነሐሴ 17/2018 ዓ.ም

የኒው ሊፍ ሜዲካል ኮምፕሌክስን መርቀን ሥራ አስጀምረናል ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ፡፡
ከንቲባዋ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ አዲስ አበባን የጤና ቱሪዝም ማዕከል እናደርጋታለን ስንል በመንግሥት ብቻ የምናሳካው ሳይሆን በግሉ ዘርፍ የሚገነቡትንም ታሳቢ በማድረግ ነው ብለዋል፡፡

ያስመረቅነው የኒው ሊፍ ሜዲካል ሆስፒታልም የዚህ አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል፡፡
ኒው ሊፍ ሜዲካል ኮምፕሌክስ በሀገራችን ከላፍቶ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ቀጥሎ ሁለተኛው PET-CT SCAN CAT LAB እና ሌሎች ዘመኑን የዋጁ ቴክኖሎጂዎች የተሟሉለት ትልቅ የጤና ማዕከል ነው ሲሉም አስረድተዋል፡፡
በጤናው ዘርፍ የምናደርገው ኢንቨስትመንት ክፍያው ከሁሉ የላቀ ስለሆነ እንደዚህ አይነት በጤናው ዘርፍ ለሚሠሩ የጤና ተቋማት እና ሆስፒታሎች ድጋፋችንን አጠናክረን እንቀጥላለንም ብለዋል።
ከንቲባዋ የኒው ሊፍ ሜዲካል ኮምፕሌክስ መስራችና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ኢማን አብዱልራህማንን እና ባለቤታቸውን አቡበከር መሃመድ ሳላህንም አመስግነዋል፡፡